Friday, August 28, 2015

ለእግዚአብሔር የተጻፈ ደብዳቤ


(ከሕጻናት ጋር በምሆንበት ጊዜ አንዲት የ9 ዓመት ልጅ አንድ ደብዳቤ ሰጠችኝ፤ መልእክቱ ለእኔ አልነበረም ለእግዚአብሔር የተጻፈ ደብዳቤ ይላል፤ ይህን ደብዳቤ እኔ ላደርሰው ፈጽሞ አልችልም እርሷ ግን ወደ እርሱ ጋር ሄዳ መልዕክቷን እንዳደረሰች አምናለሁ ከምድር ወደ እርሱ በለጋ ዕድሜዋ ሄዳለችና ይህች ሕጻን የጻፈችው መልዕክት ግን ከእኔ ጋር ነበርና ሳነበው ብዙ ነገር ያስተምረኛል . . እስቲ አናንበው . . .)


ለእግዚአብሔር የተጻፈ ደብዳቤ
ልዑል እግዚአብሔር ሆይ ለድንቅ ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ፤ ባለፈው ዓመት ወደ አንተ ጋር የመጡት አያቴ እንደምን ነች? አባዬ አንተ ጋር እንደመጡና እንደምትጠብቃቸው ነግሮኛል፤ አመሰግናለሁ አምላኬ፡፡ ደግሞ ወደ ሦስተኛ ክፍል እንዳልፍም ስለረዳኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡
እግዚአብሔር ሆይ አሁን ደብዳቤ የጻፍኩበት ትልቁ ምክንያት ማታ ማታ ጨለማ ስለምፈራ ነው፤ ጨለማ ግን ለምንድን ነው የተፈጠረው፤ ደግሞም አይጥም አፈራለሁ፤ እማማና አባባን ጠይቄያቸው ሁሉም ቦታ እግዚአብሔር ስላለ አትፍሪ ይሉኛል፤ እውነታቸውን ነው ያኛውን እኛ ቤት ያለውን እናትህ ታቅፋህ ያለውን ምስልህን ሳየው በጣም ነው ደስ የሚለኝ እሱን እያየሁ እቤት ሰው እንኳን ከሌለ አልፈራም ደግሞም አንተ የተሰቀልክበትን መስቀል አንገቴ ላይ አድርጌ በጨለማ እንኳን ስሄድ እሱን ስለማደርግ ምንም አያስፈራኝም፤ ሁሉም ቦታ እንዳለክ ደግሞ አምናለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሆይ ጨለማን እየፈራሁ ስለሆነ እባክህን ምክርህን ላክልኝ፡፡
የምወድህ ልጅህ አመተ እግዚአብሔር ነኝ፡፡







ከእግዚአብሔር የተላከ መልእክት
እጅግ የምወድሽ ውድ ልጄ አመተ እግዚአብሔር ሁል ጊዜም እኔ በጥበቃ እንደማልለይሽ ስለነገርሽኝ በአንቺ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ደግሞም እንዳትታመሚ እንደማደርግሽና ጤናሽም እንደሚጠበቅ እንደምፈልግ ልገልጽልሽ እፈልጋለሁ፤ ልጄ ሆይ፤ ጨለማን እንደምትፈሪ ነግረሽኛል እኔ ደግሞ ማታ እጅግ ለሰው ልጆች አስፈላጊ እንደሆነ ልነግርሽ አፈልጋለሁ፤ ሰዎች ቀን ሰርተው እንዲተኙ እቤታቸው ገብተው መብራቱን እንደሚያጠፉት ምሽት እጅግ ይጠቅማል፤ በስራና በትምህርት ሰዓት እንድትሰሩበት በእረፍት ጊዜ ደግሞ በጸጥታ ታርፉ ዘንድ አፈልጋለሁና፤ ደግሞም ልጄ በቁጥር የማይገለጹ መላእክቶቼን ለእናንተ ሁለት ሁለት ስለላኩላችሁ እነርሱ የማይተኙ የማያንቀላፉ ስለሆኑ ዘወትር በቀንም በማታም ይጠብቋችኋል፤ በእርግጥ ማታ በጊዜ ገብተሸ እናትና አባትሽ ጋር ተጫውተሸ እራትሽንም በልተሸ መተኛት አለብሽ፤ ሲጨልምም ዓይኖችሽ በጨለማ ማየት ስለማይችሉና እንዳትፈሪም እኔ ከፈጠርኩት እሳት ከጠቢባንም ያስገኘሁት ብርሃን ስላለ እርሱን መያዝ አለብሽ፤ እኔ በጥበቃ አልለይሽምና አትፍሪ መስቀሌን በአንገትሽ ያሺ ስትተኚና ስትነሺ ጸልዩ፤ ፍርሃት ሲሰማሽም እንዲሁ እኔም ፈጥኜ እረዳሻለሁ፡፡
የምወድሽ አባትሽ



No comments:

Post a Comment