Friday, August 28, 2015

“አባቶች ሆይ፥ . . ልጆቻችሁን አታስቆጡአቸው፡፡”



“አባቶች ሆይ፥ . .
ልጆቻችሁን አታስቆጡአቸው፡፡”
“እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው::” ኤፌ 6፡4
          ልጅ ሆኖ ያላለፈ ማንም የለም፤ ሁሉም ወጣት ከመሆኑ ከመጎልመሱና እርግናን ዘመን ከማየቱ በፊት ዳዴ ብሎ ድክ ድክ በሎ ነው ያደገው፤ በልጅነት ዘመንም መጠኑ ቢለያይም የሚያስቡልን ከአጠገባችን ያሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ልጆች ሆነን ከልዑል እግዚአብሔር ለወላጆች የተሰጠን ስጦታዎች ነንና የሚንከባከቡንን በዙሪያችን ይሰጠናል፤ መልካም ስናደርግ ያወድሱናል ስናጠፋም ይቀጡናል፤ የሚያስቡልን የሚንከባከቡን ስል ከወለዱን እናትና አባት አንስቶ አያት፣ አክስት፣ አጎት፣ ዘመድ፣ እኛን ማሳደግ አቅም ላይ የደረሱ እህትና ወንድሞቻችንን ጨምሮ ሌሎቹም ይገኙበታል፤ መጽሐፍ ቅዱስ እኚህን ልጆችን የሚንከባከቡትን ሁሉ በክብር ስም ይጠራቸዋል አምላካችን እርሱን ስንጠራው አባታችን ሆይ ብላችሁ ጥሩኝ እንዳለ ይህም ስሙ ለፍጥረቱ ያለውን እንክብካቤና አሳቢነቱን እንደሚጠቁም ሁሉ በዚሁ ስም ወላጆችን ጠርቷቿል “አባቶች ሆይ” ብሎ፡፡ አስቀድመን እንዳልነው ለልጆች አስተዳደግ በተለያየ መንገድ ከእግዚአብሔር የተመደቡለት ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ሁሉ አባቶች ናቸው፡-
አባት ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ምን ማለት ነው?
አባት ማለት ስለ ልጅ እጅግ የሚያስብ ስለ አስተዳደጉ የሚጨነቅለት፤ ሰርቶ ለፍቶ የሚመግብ፣ የሚያለብስ፣ የሚያስተምር፣ ዘወትር ርሕራሔን ለልጁ ሚያሳይ፣ ሌሎቹንም ሁሉ መስዋዕትነቱን ከፍሎ ልጁን (ልጆቹን) ደስ የሚያሰኝ ማለት ነው፡፡ ከሰፊው በጠባብ ከረጅም በአጭሩ ስንተረጉመው፡፡ ለመሆኑ በእዚህ የአባትነት መዐረግ ስም የሚጠሩት ማን ማን ናቸው ስንል ከስር የምንመለከታቸውን አካላት እናገኛለን . . .
1)   እግዚአብሔር
ከሁሉም የላቀና የበለጠ ጥበቃና አባትነት ከእግዚአብሔር ነው፤ ለዚህም ነው ከአባትም በላይ አባት አንተ ነህ ብለው ሊቃውንቱ የሚጠሩት፤ የእኛ የሰው የልጆች አባትነት ወላጅ (የወለደ / የሚወልድ) መሆን ብቻ ነው እንጂ ከዚህ ዘለን እንደ እግዚአብሔር አባትነት ፈጣሪያቸው ልንሆን ግን ከቶ አንችልም፤ ለዚህ ነው አባቶች በትምህርት ለልጆቻችን ከእኛ በላይ የሚያስብ እግዚአብሔር እንዳለ አስቡ፤ እኛም በእግዚአብሔር ፊት ልጆች ነን የምንባለው፤ የእኛ አባትነት በሥጋ እንወልዳቸዋለን አልያም በዕውቀት እንወልዳቸዋለን፤ የእግዚአብሔር አባትነት ደግሞ ፈጥሮ፣ በመላዕክቱ ጠብቆ፣ የቃሉን ወተት ከሕይወታቸው ጋር አዋሕዶ በረቂቅ ጥበቃው እየተከተለ የሚመራ ልዩ የአባትነት ጥበቃ ነው፤ እግዚአብሔርም ፍጥረታቱን ፈጥሮ የሚመግብ ፈጥሮ የሚንከባከብ አምላክ ነውና ይህንም እንክብካቤ ለሁሉም ልጆቹ ይለግሳል፤ ስለሆነም አባታችን እግዚአብሔር ስለሁሉ ያስባል፤ የሥጋ ወላጆች እንኳን በተለያየ ምክንያት ቢለዩን ለዘለዓለም የማይርቅ የማይለየን እርሱ አባታችንም እናታችንም ነው፤ በከበረና በቅዱሱ መጽሐፍ ላይ ኤር 31፡9 “እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና” ይላል፤ የእስራኤል ዘነፍስም አባት ነውና በዕለተ አርብ ከጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ በጥምቀቱ በሥጋ ከመወለድ በበለጠ ሁኔታ አዲስ በሚሆን ልደት ይወልደናል፤ መንፈሱንም አሳድሮ ከልጆቹ ጋር በመንፈስም ይተሳሰራል፡፡
የዘለአለም አባት የሰላም አለቃም ተብሎ ተጠርቷል ኢሳ 9፡6፤ ጥበቃውን የማይረሳ አባትነቱን የማይዘነጋ ሳይደክምና ሳያንቀላፋ የሚጠብቀን እርሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው፤ መዝ 120፡4 “እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም” ይላልና፤ እንዲሁም የርሕራሄ ምሳሌ የሆነች እናት የቤቱ መሠረትና ምሰሶ የተባለ አበት እንኳን ሊዘነጋ ቢችል የእርሱን ወላጅነት ሲያስረዳን “በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም፡፡” ኢሣ 49፡15 በማለት በቃል ያጸናልናል፤ ስለ እርሱ አባትነት ምንም የምንገልጽበት ቋንቋ የምንተነትንበት ቃላት የለንም፤ አባት ከልብሱ ቀዶ ያለብሳል፣ ቆርሶ ያጎርሳል፤ አምላካችን ግን ራሱ ተገፎ አለበሰን የራሱን ሥጋ ቆርሶ አበላን ከሚለው የበለጠ ስለ ልጆቹ የሚሰጥ ፍቅር መግለጫ አናገኝም፤ ዮሐ 15፡13 “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም”፡፡
2)  የነፍስ አባት (የንስሓ አባት)
የነፍስ አባቶች ካህናት አባቶቻችን ናቸው፤ እነርሱም የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር በምድር የወከላቸው እንደራሴዎቹ ናቸውና የእርሱን ጥበቃ የእርሱን እንክብካቤ የመሰለ እንክብካቤ ለልጆቻቸው ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የቅድስት ቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ መጽሐፍት ያትታሉ፤ ጌታችንም በበጎች፣ በጠቦቶች የተመሰሉ ምዕመናንን አባት ሆነው ይጠብቁ ዘንድ ስልጣንም አደራንም ሰጥቷቸዋል (ዮሐ 21፡17 )፡፡
የነፍስ አባት ወይም የንስሓ አባት አንድ ክርስቲያናዊ የሚባል ቤተሰብ ግድ ሊኖረው የሚገባ ስርዓት ነው፤ ስለሆነም ልጆች በወላጆቻቸው በኩል ንስሓ አባት ያገኛሉ፤ በሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት ከሰባት (7) ዓመታቸው በኋላ ጾምንና የንስሓ ስርዓትን የሚለማመዱበት ነውና ምንም እንኳን ኃጢያትን ባይሰሩም ለወደፊት ሕይወታቸው ስንቅና መልካም መዝገብ ይሆናቸዋልና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ይፈጽማሉ ጾሙንና ጸሎቱን ሌሎቹንም የተትሩፋትና የምግባር ሥራዎች ይለማመዳሉ፤ ስለሆነም ይህን ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲፈጽሙ ካህናቱ (የነፍስ አባት) ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፤ ከቤት ተገኝተው ጸሎት አድርገው ጸበሉን ረጭተው፣ ትምህርቱንም በምግባርና በቃል እያስተማሩ ቤተሰቡን የሚመራበትን ሕገ ቤተክርስቲያንን እየነገሩ እየመከሩና እየገሰጹ በአባትነት ያስተዳድራሉ፡፡
ይህን አባትነት የሚዘነጉ አባቶች ካሉ እንኳን አባት ሲለይ ሲሞት እንደሚያስለቅስ ቢያጠፋም አባት አባት እንደሆነ በመገንዘብ አባትነታቸውንና ኃላፊነታቸውን ግን እንዳይዘነጉ ማስታወስ ይገባል፡፡ 
3)  ክርስትና አባት ወይም እናት
ገና ከጅምሩ ስሙ እንደሚያመለክተን ለልጆች ከሚያስገልግ በቁመት ከማደግ፣ በሥጋ ከመወፈርና አልባሳትን ከማሟላት እንክብካቤ ይበልጡኑ ለነፍሳቸው እንክብካቤን ለማድረግ፤ ቀርበው የልጆችን ሚስጥራቸውን ሁሉ በማማከርና የወደ ፊት የልጆቹን ሕይወት ማቃናትና የተሻለ ማድረግ ላይ ትልቅ ኃላፊነትና ድርሻ ያላቸው ናቸው ክርስትና አባትና እናት፤ አስቀድመን እንደገለጽነው ልጆች የከበሩ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸውና ውድ ስጦታ ደግሞ ጥበቃ ስለሚገባው፤ አምላካችን እግዚአብሔር በተለያየ ዘርፍ ይጠብቋቸው ዘንድ ብዙ ባለድርሻወችን በምድር አስቀምጦለታል፤ ለቅድስት ቤተክርስቲያንም “ልጅ ተወልዶ እንደ እድሉና፤ እንደ መራው ይደግ” የሚለው አነጋገር አይስማማትም፤ ይልቁንም በተለያዩ ስርዓት ውስጥ ለጥበቃ የሚሆኑ ባለአደራ ወላጆችን ትሰጠዋለች፤ ልጆች ክርስትና ሲነሱም የልጁን አውራ ጣቱን በመያዝ ጸሎተ ሃይማኖትን በመድገም ኃላፊነትን እንዲቀበል እንዲወስድ ታደርጋለች፤ ክርስትና አባት/እናት ስለ ልጁ ክርስትናና መንፈሳዊ ሕይወት ተቀደዳሚ ተጠያቂዎች ናቸው፤ አሁን አሁን የክርስትና እናትና አባት ጥቅሙ እየተዘነጋ ኃላፊነቱም ችላ እየተባለ ስለመጣ አንጂ በዝምድና ሁሉ እጅግ የተሳሰረ ትክክለኛ የአባትና እናት እንክብካቤ ያለበት ለልጆችም ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስርዓት ነበረ ነውም፡፡
እናትና አባት እንኳን በማይኖሩበት ጊዜ እንደ እናትና አባት ቀደመው ተጠሪ የሆኑ ልጁ የነፍስ ወላጆች ናቸው እነዚሁ የክርስትና ወላጆቹ ናቸው፤ ልጁን ከመንከባከብ ባሻገር እንኳን የሥጋ ወላጆቹ የእናትና አባቱ መቸገር ልጁ ወይም ልጇ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ስላለው ችግራቸውን ለመፍታት በማንኛውን ረገድ ባለው ጉልበትም ሆነ በሃሳብ የመደገፍ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፣ እንዲሁም ከሥጋ ወላጆች ጋር ስለ ልጁና የቤተሰብ ሁኔታ ላይ መመካከርን ባለው ቅርበት ያደርጋል፤ በዋናነትም ለልጁ ወይም ልጇ የክርስትና ትምህርት ከቻለ አስተማሮ አልያም መምህራን ጋር ወስዶ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፤ አባትነት ስሙ ትልቅ እንደሆነም ሁሉ ኃላፊነቱም ትልቅ ነውና ይህን እንወጣ፡፡
4)  መምህራን
በመንፈሳዊም ይሁን በአስኳላ (አለማዊ ትምህርት) ልጆችን በዕውቀት በልጽገው የነገ ማንነታቸው የተስተካከለና የተቃና ይሆን ዘንድ መምህራን ትልቅ የቀለም አባቶች ናቸው፡፡ መምህራን ስንል በሁለት ጎራ ማየት እንችላለን፡-
4.1) መንፈሳዊ መምህሩ፡- ልጁን ለቤተሰቡ ብቻ አይደለም ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ዜጋ አድርጎ የማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውን የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምረዋል፤ 1ጢሞ 5፡4 “ልጆች አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ።” በማለት መንፈሳዊ ትምህረት እግዘአብሔርን መምሰልን ርሕራሔን ፍቅርን እንደሚያስተምርና ለወላጆችም ሆነ ውለታ ለዋሉልን ብድራትን መክፈል እንደሚማሩበት ማሕቶተ ቤተክርስቲያን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ለጢሞትዮስ ይህን መልዕክት ጽፎለታል፡፡  
4.2) የትምህረት ቤት መምህራን፡- ከወላጆች ቀጥለው ልጆችን ረዘም ላለ ሰዓት የሚያገኟቸው የአስኳላ ወይም የትምህርት ቤት አስተማሪዎች እንደሆኑ ይታወቃል፤ የተለያዩ መምህራን የተለያየ ዓላማ አላቸው በመማር ማስተማሩ ዙሪያ ለይ፤ ነገር ግን የቀለም አባት እንደመሆናችን መጠን ዋናው ኃላፊተን ዓላማችን መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል፤ ከሚከፈለን ደመወዝ በላይ ዛሬ ላይ ያልተቀበልነው የልጆቹ የነገ ተስፋ የእኛ ደሞዝ ነው፤ ሁላችንም ላለንበት ደረጃ እንድንደርስ መምህራን የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው፤ ስለሆነም የቀን ተቀን የልጆችን ውሎና ጸባይ የማጥናት ትልቅ ዕድል ያለው ሰው መምህር ነውና ልጆቹን በሚያገኛቸው ሰፋ ያለ ሰዓት የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል፤ አንዳንዴም በቤተሰብ በኩል ልጆችን የማሳደግና በሥነ-ምግባር የመቅረጽ ችግር እንኳን ቢኖር ጠርቶ ማነጋገርና በቤተሰብ በኩል ያለውን ክፍተት ጠቁሞ መቅረፍ ከሃላፊነቱ አንዱ ነው፤፤ ስለዚህ ነው መምህር አባት የሚባለው ቀደም ስንል ያነሳነውንም ኃላፊነቶች መሸከም ያለበት በዚሁ የአባትነት ኃላፊነቱ ነው፡፡
5)  ወላጅ (እናትና አባት)
ለሁላችንም ግልጽ እንደሆነ በሥጋ የወለዱ ወላጆች አባትና እናት በቅርበት ስለ ልጆች እንክብካቤ ተጠያቂ፣ ተቆርቋሪ፣ ተንከባካቢ፣ መጋቢ፣ አልባሽ፣ የመጀመሪያዎቹ አስተማሪ፣ ዋነኛ አርአያ፣ ትልቁ ተጽአኖ ፈጣሪ፣ በእነርሱም ደስ ይለን ዘንድ እግዚአብሔር ልጆችን የተወደደ ስጦታ አድርጎ የተሰጣቸው ናቸው፤ ከላይ የዘረዘርናቸው በምድር ካሉት አባቶች ውስጥም አባትነቱን የሚዘነጋ ካለ እንኳን ስለ ልጆቹ ሲል አባትነታቸውን አንዳይዘነጉና ልጆቻቸውን ለማነጽ ሱታፌን እንዲያደርጉ ማነሳሳት ማስታወስ እያተጋ የሚያቀርብ ትልቅ የልጁ አካል ወላጅ ነው፤ ከአካባቢና ከተለያየ ስፍራ በልጆች አእምሮ ክፉው መረጃ እንዳይሰለጥንባቸውና እንዳያድር ዘወትር እያረቀ መልካሙን ሥነምግባር በመቅረጽ ልጆቹን በእንክብካቤ የሚያሳድግ፤ የሚመክር የሚያስተምር ነው፤ ልጁ የተመከረውን ምክር ሳይፈጽም ከተገኝም በተለያየ ዘዴና መልኩ እግዚአብሔር የፈቀደውን መንፈሳዊ ቅጣትንና ተግሳጽ እየቀጡና እየገሰጹ እንዲያሳድጉ ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
አባቶች ሆይ!
ልጆቻችሁን አታስቆጧቸው ሲል ምን ማለቱ ነው?
ይህን ቃል እንዲሁ በጥሬው ስንመለከት የራሳችንን ትርጉምና ግንዛቤ እንይዛለን፤ ቶሎም በአእምሯችን ውስጥ አታናድዷቸው የሚል ሃሳብም ያለው ሊመስለን ይችላን፤ አንዳንዴም ልጆችን ማረምና መቅጣት እንዲሁም መገሠጽ አይገባም የሚል መልእክት የሰነቀ ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን ሐዋርያው በዚህ አውደ ንባብ ውስጥ እየተናገረን ያለው ልጆችን እንዴት አድርጎ ለመልካም ፍሬ እንደሚበቁላቸውና በእግዚአብሔር ሕግና ስርዓት በምክርና በተግሳጽ አርመን ማሳደግ እንዳለብን የሚያስገነዝብ ቃል ነው፤ ይህም አባቶች ለተባሉት ሁሉ ትልቀ ትዕዛዝ ነው፤ ይህን ሳያደርጉ ቢገኙ ልጆችን አንድም ሳንመክርና ሳንገስጽ ተንጋደውና ተበላሽተው ቢያድጉ የዓለምን ሥርዓትና ሕግን አፍርሰው ከሰው ፊት እንዳይገለሉና እነዳይቆጡ በወንጀልም ተገኝተው በምድራዊ ንጉሥ ዘንድ በሕግ እንዳይቀጡና እንዳይቆጡ ለማሳሰብ ሲሆን፤ አንድም ኋላም ሁለተኛና ዘለዓለማዊ ቅጣትና ፍርድ አለና በሠማይ ያለው የቁጣ ፍርድ እንዳያገኛው ሲል ነው፤ ለዚህም ነው ሙሉውን ዓረፍተ ነገር ስናነብ “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” የሚለው፤ ስለሆነም የተወደዳችሁ የአባትነትን ኃላፊነት የወሰዳችሁ ወላጆች ሆይ፡- ልጆችን በጌታ ምክር በቃለ እግዚአብሔር እርሱ በወንጌል ያስተማረውን በቅዱሳትም መጽሐፍት የተናገረውን ምክሮችና ትምህርቶች ገና ከልጅነታቸው እየሰጠን ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡
ይህን ኃላፊነታችነን እንድንወጣ አምላከ ቅዱሳን ሁላችንንም ይርዳን!
ይቆየን

No comments:

Post a Comment