ተረት ተረት
(ከገ/እግዚአብሔር ዘቤዛ ብዙኃን)
(ውድ አንባቢዎች ፡- ይህ ታሪክ ቁም ነገርን እንቀስምበት ዘንድ በምሳሌ የተነገረ እንጂ የፍጥረት
አፈጣጠርን እንደማይመለከት በቅድሚያ እንድትገነዘቡ ይገባል፤ ከታሪኩና ከምሳሌው ምን ቁምነገር እንደሚገኝ በማስተዋል አንብቡ
እሺ . . ፡፡)
በድሮ ዘመን ነው፤ ሁለት ክንፍ ያላቸው በራሪ የሆኑ ፍጥረታት ነበሩ፤ ንቦና ዝንቦ ይባላሉ፤
እኚህ ሁለቱ ጓደኛሞች ነበሩ፤ ንቧ በጸባይዋ የተመሰከረላትና እጅግ ትሁት ነበረች አንዲሁም ስትታዘዝ የታዘዘችውን ሁሉ ትፈጽም
ነበር፤ ሰው አታስቸግርም አትረብሽም፤ ዝንቦ ግን ንጽሕናዋን አትጠብቅም ደግሞም እየጮኸች የምታስቸግር ረባሽ ነበረች፡፡
ንቦና ዝንቦ በነበሩበት ዘመን በሀገራቸው ላይ ታላቅ ችግር መጣ ነጉሥና ንግሥቱ ቤት ሳይቀር
እጅግ ተቸገረ፤ ረሃብ ጥም በሽታም መጥቶ ብዙዎች ለሞት በቁ፤ ንቦና ዝንቦ የሚኖሩት በቤተ መንግሥት ውስጥ ንጉሡንና ንግሥቲቱን
ስለሆነ ችግሩ የሀገር ችግር ስለሆነ በደንብ የተፈጠረውን ነገር ሁል ጊዜ ይሰሙ ነበር፤ ከዕለታት አንድ ቀን ንቦና ዝንቦ ከቤተ
መንግሥቱ ፊት ለፊት ባለ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ቁጭ ብለው ስለ ተፈጠረው የሀገራቸውና የተከበረ የቤተመንግሥታቸው ችግር ላይ ያወጉ
ወይም ያወሩ ነበር፤ “ምን ይሻለናል አሁን” አለች ንቢት የሚያምር ንዝረት ያለውን ድምጻን እያሰማች፤ “በዚህ ሁኔታ እኮ
ከቀጠለ ሕዝባችን ሁሉ ማለቁ ነው፤ ማን ይሆን ነገ ላይ ሀገርና ታላቁን ቤተ መንግሥታችንን ተረክቦ የሚኖረው?” እያለች በሀዘን
አለቀሰች፤ ዝንቦም “እኔ ደግሞ በጣም የጨነቀኝ ነገ እኛም እንዳንራብ እንዳንጠማ ነው፡፡” አለች በጸጸትና በፍረሀት፤ “የታላቁ
ቤተመንግሥታችን ክብርስ አያሳስብሽም?” አለች ንቢት እንባዋን ጠራርጋ፤ ዝንቢትም “አይ ክብር እሱማ ቢኖር ጥሩ ነበር እኔ ግን
በቅድሚያ የሚያሳስበኝ የእኔ ጉዳይ ነው፤ እኔ እንዲርበኝ አልፈልግም እንደውም ያሉት ሕዝቦች በዝተው ያለው እህል አልቆ
ከምንራብ ሌሎቹ ሰዎች ወደ ሌላ ሀገር ቢሰደዱ ጥሩ ነበር፡፡” ብላ በድፍረት ተናገረች፤ ንቢት በጣም ደነገጠች ተናደደችም
“እንዴት እንዲህ ትያለሽ፤ አብረን ያለንን ተካፍለን እንበላለን እንጂ ለምን ይሰደዳሉ፤ ደግሞስ ለዛሬ ቢርበን ለነገው ሕዝባችን
እናስብ እንጂ . . ” እያለች ስታወራ ከአፏ ቀማቻትና፤ “በይ በይ እኔ ለራሴ መኖር ነው የምፈልገው የታላቁ ቤተመንግሥት፣
የሀገሬና ወገኔ ችግር ከእኔ በፊት አያስጨንቀኝም፤ ይልቅ መላ እንፈልግና ከዚህ ችግር እንዴት እንደምንጣ ዘዴ እንቀይስ”
አለቻት፤ ንቢትም ቀጠል አድርጋ “እኔ እኮ እሱን ልልሽ ነበር እዚህም እንድንጫወት ያልኩሽ፤ እኔ ጋር አንድ መላ ነበረኝ፡፡”
አለቻት፤ ዝንቢት መላና ዘዴውን ለመስማት ጓጓች፤ “ምንድን ነው የመጣልሽ በጎ ሃሳብ?” አለቻት ወደ እርሷ ዞራ፤ “ይሄውልሽ
ውድ ጓደኛዬ፤ ይሄን ችግር ሊቀርፍልን የሚችል አንድ ታላቅ ኃይል ያለው የንጉሦች ሁሉ ንጉሥ የሆነ፤ ሩሕ ሩሕ ደግ አባት አለ”
አለቻት፤ “ማን ነው እሱ?” ብላ በድጋሚ ጠየቀች ዝንቧ፤ “አታውቂውም ፈጣሪያችን ነዋ፤ ከእርሱ በቀር የሕዝባችንን ችግር፤
የንጉሣችንንና ንግሥታችንን ጭንቀት ሊፈታ የሚችል ማንም የለም! ሰለዚህ ፈጥነን ወደ እርሱ ጋር በረን መሄድ አለብን” ብላ ወደ
ሰማይ አሻቅባ አየች፤ ዝንቦም “ታዲያ አሁኑኑ እንሂዳ” አለችና አብረው ተያይዘው በረሩ፡፡
ታላቁ የሠማይ ቤተመንግሥት ሲደርሱ የቤተመንግሥቱ አቀማመጥና አሠራር ልክ ሀገራቸው እንዳለው
ታላቁ ቤተመንግሥትን ይመስላል፤ እዚህ ግን ምንም ችግር የለም ደስ የሚል መዝሙርም ይሰማበታል የሚያገለግሉትም ረቂቅና ኃያላን
የሆኑ መላእክት ናቸው፤ ወደ ውስጥ እንደ ሐር ግምጃ የተነጠፈውን የሚያምር አረንጓዴ ምንጣፍ እየለሰለሳቸው እየረገጡ በፍርሃት
ገቡ፤ በሠማዩ ቤተመንግሥትም በደመና የተከበበ የሚመስል በታላቅ ዙፋን ላይ የተቀመጠ መልኩ በጣም የሚያምርና ደስ የሚል ግርማው
የሚያስፈራም ንጉሥ ተመለከቱ፤ እርሱም እጆቹን ዘርግቶ ወደ እርሱ አቀረባቸውና፤ “ምን ትሻላችሁ?” ብሎ በርህራሄ ጠየቃቸው፤
ንቢትም በግንባሯ ተደፍታ እያለቀሰች በሀገሯና በቤተመንግሥታቸው የገጠማቸውን ችግር፤ ተናገረች፤ ዝንብ ግን በልቧ አንዲህ
እያለች ታስብ ነበር፤ “እኔን እዚሁ አስቀረኝ፤ ወደ እዛ ችግር ወደ ጸናበት ሀገሬ አትመልሰኝ ብዬ ልለምን እንዴ?” ብላ በልቧ
ታመላልስ ነበር፤ በግንባሯም ወድቃ አልሰገደችም ነበር፤ ያም የነገሥታት ሁሉ ንጉሥ ንቧን በአገልጋዩ መልአክ አጽናንት
አስነሳት፤ ወደ ዝንቢትም ተመልክቶ “አንቺ ግን ስለምን እዚህ መቅረትን አሰብሽ?” አላት፤ እርሷ ደግም በመደነቅ መልሱን
መመለስ ትታ “እንዴ ያልተናገርኩትን እንዴት አወቅክ?” አለች፤ ከዙሪያው ካሉ አገልጋይ መልአክ አንዱም “ሁሉን የሚያውቅ
የተሰወረው የሚገለጽለት የአማልክት አምላክ ሆይ ክብር ምስጋና ላንተ ይገባል፡፡” ብሎ አወጀ፤ መልአኩም ቀጥሎ እንዲህ አለ፤ “ደግሞም
ወደ ችግረኞቹ ወገኖችሽ አትመልሰኝ ብለሽም
አስበሻል” አላት፤ በዚህን ጊዜ ዝንቢት
በልቧ የታሰበውን እንኳን ንጉሡ አገልጋዩ ታላቁ መልአክ እንዳወቀባት አየችና አንገቷን ደፍታ ዝም አለች፡፡
ንጉሡም እንዲህ ብሎ መናገር ጀመረ፤ “የተወደዳችሁ ፍጥረቶቼ ሆይ፤ እኔ ለተፈጠረው ችግራችሁ ሁሉ
አዝንላችሁ ነበር፤ ጉዳዩንም አውቃለሁ፤ ይህንም ችግር ላስወግድላችሁ ቃል እገባላችኋለሁ” አላቸው፤ በዚህን ጊዜ የሁለቱም ፊት
በተስፋ ብርሃን አበራ፤ “ነገር ግን በቅድሚያ. .” ሲል ሁለቱም የቀደመው ደስታን በልባቸው እንደያዙት ጆሮአቸውን በአትኩሮት
ከቀደመው ይልቅ ከፍተው ቀጣዩን ለማድመጥ ጓጉ፤ “ነገር ግን ይህን ከማድረጌ በቅድሚያ አንድ የማዝዛችሁ ትዕዛዝ አለ፤ ንቢት
የንግሥቲቷ አገልጋይ ዝንቢት ደግሞ የንጉሡ ወይን አቅራቢ መሆናችሁን አውቃለሁ፤ ስለሆነም በቅድሚያ ሄዳችሁ በሚመጣው በሦስት
ቀን ውስጥ ንቢት ንግሥትሽ
በጣም የምትወደውና የምታምር ጌጥ እንዳላት ታውቂያለሽ እሱን ሳትሰማ ሰርቀሽ እንድታመጪ፤ ዝንቢትም ንጉሥሽ አውልቆት
የማያውቀውን ዘውድ ይዘሽ እንድታመጪ እፈልጋለሁ፤ ይህን ካደረጋችሁ ችግራችሁ ሁሉ ይጠፋላችኋል ንጉሥም ሆናችሁ ትሾማላችሁ፡፡”
ብሎ የሚያስደነግጥ ነገር ነገራቸው፤ ምክንያቱም ንግሥቷ እንቁ የተባለ ጌጧን ካጣች ቶሞታለች፤ ንጉሡም ዘውዱ ከወለቀበት
ንግሥናው ተሽሮ ጠላቶቹ ያሸንፉትና ይሞታልና ነው፡፡
ብዙ ቢያወሩም ይህን ትዕዛዝ ግን ተቀብለው ከታላቁ ሠማያዊ ቤተ መንግሥት ወጡ፤ ሁለቱም ቅዝዝ
ብለው ነው የሚራመዱት፤ ንቢት “እንዴት ንግሥቴ ትሞትብኛለች?” ትላለች፤ ዝንቢት ደግሞ “እንዴት ደፍሬ ያን የተከበረ የንጉሥ
ዘውድ አውልቄ ማምጣት እችላለሁ?” ብላ ታስባለች፡፡ ንቧ እንዲህ ብላ አሰበች “ይህን ከማደርግና ንግሥቴ ከምትሞት ባላደርገው
እመርጣለሁ ደግሞ ችግሩ ተባብሷል የግድ በዚህ ዓመት መፍትሄ ካላገኘን ሁላችንም እንሞታለን፤” እያለች በሁለት ሃሳብ ተወጠረች፤
ግን አንድ ሃሳብ መጣላት “ለምን ግን እኔ ያለኝን ሁሉ ሸጬ፤ ራሴንም ቢሆን ለዘለዓለም ሰራተኛ ሆኜ አገለግላለሁ ብዬ ብዙ ብር
ተበድሬ ያን የሚያችል ውድ ዕንቁ ገዝቼ መምጣት አለብኝ” ብላ ወደ ቤቷ በፍጥነት በረረች፤ ዝንቦም “የታላቁ ንጉሥ ወይን
አቅራቢ አይደለሁ ዛሬ በጣም የሚያሰክር የወይን ጠጅን ለንጉሡ ሰጥቼ ዘውዱን እንደምንም ደብቄ መምጣት አለብኝ” ብላ ወደ ቤተ
መንግሥቱ የወይን መጥመቂያ ቤት በረረች፡፡
ከሦስት ቀን በኋላ ሁለቱም ለየ ብቻ ሆነው ወደ ሠማያዊው ታላቁ ቤተ መንግሥት በቀጠሯቸው መሠረት
ቀረቡ፤ በቅድሚያ ለክብር ተጣድፋ ዝንቧ ዘውዱን ይዛ ሮጣ ለሰማያዊው ንጉሥ እያቀረበች “ይኸው ንጉሣችን ሆይ ያልከውን
አመጣሁልህ” አለች፤ ንቢት ይህን ስትመለከት እጅግ በጣም አለቀሰች ንጉሣቸው በጠላት ወዲያውኑ እንደሚሞት ስላወቀች፤ አሁንም
ታላቁ የሰላም ንጉሥ አጽናንቷት፤ “አንቺስ ምን ይዘሽ መጣሽ?” አላት፤ እርሷም አሁንም በግንባሯ በትህትና ተደፍታ፤ “አምላኬ፤
አንተን ሁሉን የምታውቅ የማይዋሹህ እውነተኛ ንጉሥ ነህ፤ እኔ የንግሥቴን ሞት ስለማልፈልግ የንግሥቴን ዕንቁ ላመጣ አልቻልኩም
ሕሊናዬ አልፈቀደምና፤ ነገር ግን አማላኬ ሆይ ዕድሜ ልኬን እንደ ባርያ አንድ ባለ ሃብት ጋር እንደምሰራለት ያንም ዕድሜ ልክ
ሊከፍለኝ የሚችለውን ብር እኔ ግን የሌለኝን ሰጠኝ ያለኝን ሃብትና ንብረትም ሸጬ ጨመርኩበትና የንግሥቴን ዕንቁ ጋር እኩል
የሆነ ዕንቁ አምጥቼአለሁ፡፡” ብላ እጆቿን በክብር ዘረጋች፤ ያም ንጉሥ ከዙፋኑ ቆሞ ያችን ትሁት ንብ አመሰገናት፤ እንዲህም
አላት “አንቺ የተባረችሽ ልጅ፡- ለወገኖችሽ አሳቢና ለንግሥትሽም ተቆርቋሪ ነሽ ለሀገርሽ እንዳሰብሽ ችግሩን ሁሉ ከአሁን
ሰከንድ በኋላ ሀገርሽ ስትገቢ ርቆ ታገኚዋለሽ አንቺም በያዝሽው ውድ ዕንቆ ቀጥለሽ አነግሥሻለሁ ከአንቺም በኋላ ላሉት ዘሮችሽ፤
በሚያምርና መአዛው በሚያውድ አበባ እንድትኖሪ አደርግሻለሁ ብዙ ሠራተኛና ወታደር ንቦችን አስገዛልሻለሁ፤ በአንቺም ዘሮች
ከሰራተኞችሽም ጣፋጭ ማር እንዲገኝ አደርጋለሁ ረሃብም አይኖርባችሁም የህመምም ማራችሁን ፈውስን እንዲሰጥ አደርገዋለሁ፤ ጠላትን
የምትከላከሉበት መንደፊያ እሰጣችኋለሁ፡፡” ብሎ ባረካት፤ ወደ ዝንቢትም ዞሮ፡- “አንቺ ግን ለፈተና ዘውድ አምጪልኝ ስልሽ
እንኳን ውስጥሽ መልካም ሃሳብ አልነበረምና ለምን አላልሽም፤ ደግሞም ሩህ ሩህነቴን ታውቂ የለምን? ስለምን እንዲህ አዘዘኝ
ብለሽ ደግሞም እንደ ንቢት ራሴን መስዋዕት አድርጌ ሌላ ባቀርብ ይቀበለኛል ብለሽ አላመንሽብኝም፤ ደግሞም ንጉሥሽን አታለሽ
አስክረሽ ዘውዱን ሰርቀሻል ስለሆነም ከትዕዛዜ አትዋሽ፣
አትስረቅ፣ በሌላው ላይ ክፉ አታድርግ የሚለውንና ሌላውንም ትዕዛዜን አፍርሰሻልና መኖሪያሽ የቆሸሸ ቦታ ይሆናል፤ በገባሽበትም ቦታ
በጭራ ያባርሩሻል አንቺ ቆሻሻ ላይ ስለምትውዬ በሽታን ታመጪባቸዋለሽና፡፡” ብሎ ተቆጥቷት ሁለቱም ወደ ሃገራቸው ተመለሱ ሀገራቸው
ላይ ያለው ችግር ሁሉ ጠፍቶ ነበር፤ ነገር ግን ንቢት ስትደርስ ደስ የሚል ክብና የተለያየ ቅርጽ እየሰራች ጢዝዝ እያለች እየበረረች
ስለ ንጉሡ ታለቅስ ነበር፤ እንደ አምላኳ ትዕዛዝ ሦስት ጊዜ አለቀሰች በኋላም ሌላ ንጉሥን አምላክ ተካላቸውና እርሷም ልዕልት ሆና
ወደ በቤተመንግሥቱ ውስጥ ገባች ከዚያም ሁሉም በሰላም መኖር ጀመሩ፡፡
አሁን የተረክነውን ታረክ የመሰለ ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታ ታገኛላችሁ፤
ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲገባን ደስ በሚሉ ታሪኮችና ምሳሌዎች ነበር ያስተማረው፤ ነገር ግን የእመቤታቸን ልጆች
ሆይ፤ ከታሪክና ከምሳሌ በስተ ጀርባ ብዙ ቁም ነገርና ምስጢር እንዳለ ማወቅና መገንዘብ ይኖርብናል፤ ለምሳሌ ልጆችዬ ይህን ታሪክ
ላነበቡላችሁ ታላላቆቻችሁ ወይም ወላጆቻችሁ ሀገር የተባለችውን ኢትዮጵያ፤ ታላቋ ቤተመንግሥት የተባለችውን ቤተክርስቲያን ንጉሥ የታለውን
የቤተክርስቲያን ክብር ንግሥት የተባለችውን ሁሌም አዳዲስ ትርጓሜያትን በምትወልድ የማያልቅ የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ (ትምህርት)
፤ ንብና ንቢት የተባሉት ደግሞ ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የሚገባቸውን ልጆቿ ምሳሌ አድርጋችሁ መስላችሁ እንዲነግሯችሁና እንዲያወሩላችሁ
ጥይቋቸው፤ በቅድሚያም ምሳሌ ምን ማለት እንደሆነ ያብራሩላችኋል፡፡ በሉ እንግዲህ እንደ ንቢቷ መልካም እንድንሰራ ልዑል እግዚአብሔር
ይርዳን ምሥጋናም ለእርሱ ይሁን፤ ደህና ሁኑ . . .
ወስብሐት ለእግዚአብሔር