Wednesday, January 6, 2016

ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡” ኢሣ 9፡6

ልዑል እግዚአብሔር ለዓለሙ ለተፈጥሮ ሁሉ ውብና ድንቅ ሊቆጠሩ የማይችሉ እልፍ ስጦታዎችን አድሏል፤ ለእኛ ለሰው ልጆች ደግሞ በይበልጥ ከአፈጣጠራችን አንስቶ ሊነገሩ የማይችሉ ስጦታዎችን ቸሮናል፤ ለዚሁ ነው ቅዱስ አባታችን ዳዊት በመዝሙሩ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” መዝ 8፡4 ይህንኑ ተፈጥሮውን ሲያመሰግን “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፡፡” መዝ 138፡14 ይላል፡፡
ይህ ሁሉ ስጦታ ሊነገር የማይችል ከእግዚአብሔር ለእኛ የተደረገ ነው፤ ከሁሉ የበለጠውን ስጦታ ግን የሚያምረውን አፍላግ፤ የጠራውን ሰማይ፤ መንፈስን የሚያስደስት የተፈጥሮን ውበት፤ ደስታን፤ ማስተዋልን፤ ጥበብን፤ ሕያውነትን ሌሎቹንም ከመስጠቱ የሚበልጠው የወርቃማው ዘመን ቅዱሳን ሊቃውንት እንደጻፉልን እግዚአብሔር ለሰው ከሰጠው ስጦታ ሁሉ ራሱን የሰጠን ስጦታ ከሁሉ ይበልጣል፤ ዓለምን ከፈጠረበትም ጥበቡ ይልቅ ዓለሙን ያዳነበት ጥበቡ ይልቃል ይላሉ፤ እውነት ነው፡፡
ውድ የእግአብሔር ቤተሰቦች፤ ነቢዩ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል እንዳለ የዛሬው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት (የገና) በዓል የስጦታ በዓል ነው፤ በልዕልና በክብር ይኖር የነበረ አምላክ ለእኛ መድኃኒት ሊሆን የተሰጠበት፤ ጨለማውን በብርሃኑ ሊገፍልን ከምድር የወደቅነውን አንስቶ ወደ ሰማያዊ ክብር ከፍ ሊያደርገን እግዚአብሔር እንዲሁ ወድዶን ራሱን የሰጠበት፤ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡” ዮሐ 3፡16፤ እንዳለ፡፡
ወደ ኋላ ጌታችን የተወለደባትን ቀን በጥቂቱ እስቲ እናስብ፡- እመብርሃን ወላዲተ አምላክ እርሱን በማኅጸኗ ተሸክማ በአዋጅ በተነገረው ቆጠራ ወጥታ ስትንከራተት እግዚአብሔር ለሰዎች እንዲኖሩበት የሰጣቸውን ቤታቸውን ነፈጓት፤ ለእርሱም ማደርያ አጣ፤ ዮሴፍ ቅዱሱም ጌታን በማኅጸኗ የያዘችውን ክብርት እናት ይዞ ጨለማው በበረታበት ወቅት ማደርያ ፍለጋ ተንከራተተ፤ በሰዎች ቤት ቦታን አጣ ጌታችንም በእመቤታችን ማኅጸን ሆኖ የሚቀበለውን አጣ፤ ዛሬም እኛ በልባችን ጓዳ እናቱን ለመቀበል እርሱንና ቅዱሱን ለማሳረፍ ቦታ አለን ወይ? ዓለም በቤተልሔም ከእናቱ ጋር ካለው በጨርቅ ተጠቅልሎ ከተኛው ከሕጻኑ ጋር ልደቱን ስታከር አትታይም፤ ይልቁንም ብርሃነ ልደቱን ምክንያት በማድረግ በጨለማ ሞተ ኃጢያት ይዳክራል፤ ዘፈንና ስካርን ይመርጣል፤ ይህም ዮሐ 1፡11 “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም፡፡” የተባለው ቃል መፈጸሚያ ነው፤ እርሱ ለእኛ ሲሰጥ ቤት ልባችንን ልንነፍገው አይገባም! ምንም እንኳን እንደ ከብቶቹ በረት የቆሸሸ ቢሆን፤ መዐዛው የማያምር ቢሆንም፤ እርሱ አምላካችን ከእናቱና ከቅዱሳኑ ጋር ሲገባበት መላእክቱ ከገነት በዚህ ዓለም በየትኛውም ጠቢብ ሊቀምመው የማይችለውን ጥዑም መዓዛ ያለውን ሽቱ ያርከፈክፉበታል፤ ግርግሙ ጉድጓድ ሆኖ ጨለማ ቢሆንም ብርሃናውያን መላዕክት ይወርዱበታል፤ ስለዚህም ከእንቁ ያበራል፡፡
በዚያች ዕለት በቤተልሔም ከዘጠና ዘጠኙ ነገድ ማንም የቀረ የለም ቤተልሔም በብርሃን ጎርፍ ተጥለቅልቃለች፤ ደስታ ሆኗል መላዕክት ከእረኞች ጋር ዘምረዋል በአርያም የነበረው ምስጋና በምድርም ተደረገ፤ ያቺ ቤተልሔም አርያምን መስላለች፤ ውድ የበዓሉ በረከትና ስጦታ ተካፋዮች ሆይ! ልቦናችን ልጁን ከእናቱ ጋር ሊቀበል ይዘጋጅ እርሱም በብርሃን ይመላል፤ ክፉ የኃጢያት መዓዛው በመልካም ይለወጣል፤ መላእክት የሚወጡበት የሚወርዱበት እንደ ያዕቆብ መሰላል አይነት ይሆንልናል፤ የዛኔ ጸሎታችን ያርጋል በረከትም ይወርዳል፡፡
ልደት የስጦታ በዓል ነው:: አምላክ ለእኛ ለሰው ልጆች የተሰጠበት፤ ከእኛም ደግሞ ስጦታ ያስፈልጋል፤ ለአምላክ የምንሰጠው ስጦታ ምንድን ነው? እንደ ወርቅ የጠራ ንጽሕናችንን? እንደ እጣን መልካም መአዛ ያለው ሕይወታችን? ወይስ እንደ ከርቤ የፍቅር መስዋዕትነትንና በፈተና መጽናትን? እኚህ ስጦታዎች ከእኛ ደግሞ ይጠበቃሉ፤ አገልግሎት ስጦታ ነው፤ ንጽሕና ቅድስና ስጦታ ነው፤ መጸለይ ስጦታ ነው፤ መዘመር ስጦታ ነው፤ ቅዱስ ቃሉን መስማት ስጦታ ነው፤ ልቦናችንን ለእግዚአብሔር መስጠት የእርሱ ማደርያ እንዲሆን ማድረግ ደግሞ ታላቅ ስጦታ ነው፤ ምሳ 23፡26 “ልብህን ስጠኝ፡፡” ይላልና ልዑል እግዚአብሔር፡፡ ሰውነታችን ቅዱስ መስዋእት ሆኖ ለእግዚአብሔር እንዲቀርብ ብንተጋ ተሰጥቶ በልቶ ቀሮች አንዳንሆን ያደርገናል፤ ብዙ ተሰጥቶን በጥቂቱ መስጠቱ አይከብደንም ያለችንን ከኪሳችን ሳይሆን ከውስጣችን ውስጣችንን እንስጥ፤ እርሱ ይህን ያህል ውለታና ስጦታ አድርጎልን፤ ይህን ያህል ፍቅሩን ገልጾልን የእኛ ደግሞ በጥቂቱ የቻልነውን እንስጥ፤ ለደከሙት ብርታትን እንዲያገኙ መጽናናትን እንስጥ፤ ግራ ለተጋቡ ምክራችንን እንስጥ፤ ፍቅር ላጡት ፍቅርን እንስጥ፤ ወገን ዘመድ ቤተሰብ ለሌላቸው የራሳችን ቤተሰባዊነታችንን እንስት፤ እርቅ ለሚሹ ይቅርታን እንስጥ፤ . . . እንስጥ ፣ . . እንስጥ፤ ለዛውም በመስጠታችን ውስጥም ለመሰጠት (ሊሰጠን!!)፡፡
በልደቱ በዓል የተሰጠን ቅዱሱ ሕጻን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋር ሆኖ ወደ ቤታችን ይግባልን፤ በዓሉንም የበረከት በዓል ለሁላችንም ያድርግልን፡፡

No comments:

Post a Comment