በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“ወንድሞች
ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ
ዘንድ ፈቀቅ በሉ፡፡”
ሮሜ 16፡17
5ቱ ብቻዎች
በቅድስት
ቤተክርስትያናችን አስተምህሮ በመንፈሳዊ ጎዳና ለመጓዝና መንግሥቱን ለመውረስ ልዩ ልዩ የሆኑ የምግባርና የትሩፋት ስራዎችን በእምነት
ውስጥ ሁነን ልንተገብር እንደሚገባ ታስተምረናለች፡፡
አምላካችን
እግዚአብሔርም እኛን ደካማ ልጆቹን ለማዳን በልዩ ልዩ ምክንያት እንደሚደግፈንና እንደሚያግዘን ምክንያተ ድኅነትንም አብዝቶ የድኅነትንም
መንገድ እንደሚጠቁመን እንማራለን፤
እግዚአብሔር
እኛን ለማዳን ያለው ጥበብና መንገድ እኚህ ብቻ ናቸው ብሎ መወሰን ሁሉን ቻዩን እግዚአብሔርን በከለልነው አጥር መወሰናችን ነው፤
ከሃሊነቱንም መጠራጠር ነው፡፡ ክርስትናም ብቻ ከሚለው አገላለጽ እጅግ የራቀና ወንድሞች በሕብረት ቢኖሩ መልካም ነው ብላ ሰብስባ
ለዚህ ብቻ አይደለም መልካም ምግባራትንና የእምነት መሰረቶችንም በአንድነት ሰብስባ የምትይዝ ያጌጠች እመቤት ናት ቤተክርስቲያናችን፡፡
ሐዋርየት
በትምህርታቸው አብዝተን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሆኑትንና መልካም ምግባራትን ሁሉ ልንይዝ አንደሚገባ ያስተምሩናል፤ ማሕቶተ ቤተክርስቲያን
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከው መልዕክቱ በእምነትም በምግባራቸውም በመልካም ንግግራቸው እንዲሁም በመንፈሳዊ
እውቀትና ትጋት በማሳየታቸው ያመሰገናቸውና ይህንንም አሁንም አብዙት ይላቸውል፡፡
“በሁሉ ነገር
በእምነትና በቃል በዕውቀትም በትጋትም በእናንተ ዘንድ በሆነው
ሁሉ እኛን በመውደዳችሁ ፍጹማን እንደ ሆናችሁ እንዲሁም ደግሞ
ይህቺን ስጦታ አብዙ፡፡” 2ቆሮ 8፡7 ብሏል ስለሆነም በብዙ
ጎዳናና ሕብረ አምሳል ከነብያቱ ጀምሮ ይገለጽ የነበረ አምላካችን ድኅነቱንም በብዙ ጎዳና እንዲፈጸም ፈቅዷል፡፡
በመናፍቃን
ጎራ ግን የድኅነትን ስራ በተወሰኑ ነገሮች ብቻ ገድበው ሲያቀርቡ እንመለከታለን፤ ከእነዚህም ውስጥ አምስቱ ብቻዎች የሚሉት አስተምህሮት
አብዛኞቹ የሚስማሙበትና እንደ እምነታቸውም መሰረት አድርገው የተቀበሏቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በታች በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡
5ቱ ብቻዎች
በይበልጥ
በምዕራባውያኑ የእምነት ድርጅቶች በስፋት ደግሞም በአውሮፓያኑ የሃይማኖት አስተምህሮ የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴና የተሃድሶ አራማጆች
ላይ ትልቁን ስፍራና ማዕከል ይዘው የሚገኙ ናቸው እኚህ 5ቱ ብቻዎች፡፡ 5ቱ ብቻዎች ስንል እምነታቸውን ለመምራት እንዲሁም አንድ
ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ በዋነኝነት እንዚህን 5 ነገሮችን ብቻ ሌላ ሳይቀላቅል መፈጸም ለጸድቅ እንደሚያበቃ ይናገራሉ፤
በተጨማሪም ከእንዚህ ውጪ መጨመር ወይም ማድረግ እንደ ክህደትና ከመንግስቱ የሚከለክል ተግባር ነው ብለውም ያምናሉ፡፡ በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ ብዙ አምስት ነገሮችን እናገኛለን ዛሬ የምናያቸው ግን ከነዚህ የተለዩናቸው፡፡
እነዚህ
አምስቱ ብቻዎች የተሰኙትም
1- በመጽሐፍ ብቻ Sola Scriptura “by
scripture alone”
2- ክርስቶስ ብቻ Sola christus or Solo Christo
“Christ alone”
3- በጸጋው ብቻ Sola
Gratia “by grace alone”
4- እምነት ብቻ Sola
Fide “by faith alone”
5- ምስጋና ለእግዚአብሔር ብቻ Sola Deogloria “Glory to
God alone” ናቸው፡፡
እኚህን
በቅደም ተከተል ከመመልከታችን በፊት በእያንዳንዱ ዝርዝር ላይ በላቲኑ ቃል ሶላ ‘Sola’ የሚል ቃል በተደጋጋሚ እናገኛለን፤ ይህ
ቃል ትርጉሙ ብቻ ከሚለው የአማረኛችን ቃል ጠንከር ያለና ሌላ ተጨማሪ ነገር ፈጽሞ የማያስፈልገው ብቸኛ የሚል ትርጓሜ አለው፤ አባታችን
አብርሃም በሰዶም ለነበሩ ሰዎች በምልጃ እግዚአብሔርን ሲለምንላቸው የተናገረው አንድ ቃል አለ፤ “እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር
ጌታዬ አይቆጣ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ? አለ፡፡” በዚህ ቃል አገባብ አንድ ጊዜ ብቻ ብሎ አባታችን አብርሃም ከእግዚአብሔር
ጋር ብዙ ጊዜ በሰዶም ውስጥ ጻድቃንን ለማግኘት የተደረገ ንግግር ነበረ፤ በዚህ አገባብ አንድ ጊዜ ብቻ የተባለው እንደ ላይኛው
አገባብ አይደለም፡፡ ልክ በዘፍ 27፡38 ኤሳው ይሕሳቅን “አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን?” እንዳለው ዳግመኛ እንደማይሰጠው
ቡራኬ አድርገው ብቸኝነቱን ይገልጻሉ፡፡
በጣም
የሚገርመው አምስት ብቻ መሆናቸው ሳይሆን እያንዳንዱም ሲተገበሩ ብቻቸውን መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ የተዘረዘሩትን በብቸኝነት
መፈጸም ከ5ቱም ሳይጨምሩባቸው እንዲሁም እያንዳንዱንም ሲፈጽሙ ሌላ የትሩፋትና የምግባር ስራ ማከል ሳያስፈልጋቸው ይፈጸሙ ይላሉ፡፡
የ5ቱ ብቻዎች አስተምህሮ ጽንሰ
ሐሳብ ጅማሮ
በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው
ጀርመናዊው ማርቲን ሉተር የዚህ ጽንሰ ሐሳብ ጅማሮ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገራል፤ ማርቲን ሉተር በጣልያን ግዛት ቅድስቱ
ከተማ በተባለችው የሮማ ግዛት በ1483 እ.ኢ.አ ከሁለቱ ካቶሊካውን ቤተሰቦቹ የተገኘ ሲሆን፤ ከዕለታት አንድ ቀንም ባጋጠመው የመብረቅ
አደጋ በመሳቱ ምክንያት በመደንገጡ ወደ በካቶሊካውያኑ የምንኩስና ሕይወት ሊገባ ችሏል፤ ፍቅረ እግዚአብሔር ስቦትና የምንኩስና ሕይወት
ገብቶት ነው ወይ ይህን የሕይወት መንገድ የመረጠው የሚለው ላይ ትልቅ ጥያቄ አለ እዚህ ላይ፡፡ ምንኩስና የስጋን ሞት ሳይሆን ከነፍስ
ሞት ለመዳን የሚመረጥ ውድና ታላቅ የተጋድሎ ሕይወት ነውና፤ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቀጥሎ ቀደምት ከሚባሉት የሐዋርያትን
የአባቶች ትውፊት ምንም ቢሆን ለዛው አለቀቀባቸውም በተባሉበት የካቶሊክ የገዳም ስርዓት ስለሆነ የገባው ለሥጋ ከባድ የሆነውን የጾም፣
የጸሎትና የድንግልና ሕይወት መፈጸሙ ግድ ሆኖበት ነበር፤ በስነ መለኮት ትምህርትም በዊተንበርግ ዩኒቨርሲቲ የመጽሐፍት ትምህርትን
እንደተማረ ይነገራል፡፡
ማርቲን ሉተር በዚህ መሰል ኑሮ
በሚሄድበት ወቅት በካቶሊካውያን መሪዎችና አስተዳደር ሰዎች ይፈጸሙ የነበሩ በደሎችን ይመለከት ነበር፤ ተመልክቶም አልቀረም ለችግሮቹ
እዛው እንዳለ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ወደ 1520ዎቹ ገደማ በውስጡ ለዘመናት ያጠራቀመውን ተቃውሞ አወጣው፤ በዚያን ወቅት ከነበሩት
የተቃውሞው ምክንያቶች አንዱ ካቶሊካውያኑ በሮም በቫቲካን ከተማ እንገነባዋለን ያሉት የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በዋነኝነት ይነሳል፤
የሮማ ቤተክርስቲያንም ይህን ካቴድራል ዓለምን በሚያስገርም መልኩ እጹብ ድንቅ አድርጌ አንጸዋለሁ ብላ ገንዘብ ማሰባሰቧን ተያያዘችው፤
ነገር ግን ሕንጻው ይፈልግ የነበረውን በመጠኑ በጣም ከፍ ያለ ገንዘብ እንዲሁ በቀላሉ ስለማይገኝ የተለያዩ ጥበቦችና መንገዶችን
በማየት ገንዘቡን ለማሰባሰብ ሞክረዋል ከእነዚህም መካከል መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባ የሰማያዊው ካርድ ሽያጭ ይጠቀሳል፤ እንዲሁ
እንደቀልድ ለገንዘብ ማሰባሰቢያ የተነሳው የዚህ ካርድ ሽያጭ ካቶሊካውያኑ ልክ እንደ ሃይማኖት የምግባር ብቻ ሳይሆኑ ግድ ሊፈጽሙት
እንደሚገባ አድርጋ ማስተማርዋ ትልቁን ችግር ፈጥሮ ነበር ይህም ሃሳብ ድልብ ገንዘብ ያለቸው ባለጸጎችን ያስደሰተ ሲሆን መጠነኛና
አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትን ምእመናኖቻቸውን ግን እጅጉን አስቆጥቶ ነበር፤ የምግባርና የትሩፋት ስራ
መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ የሚደረግ ብዙ ተጋድሎን በአንድ ካርድ ግዢ ማስተካከሉ እውነትም ትልቅ ስህተት ነበረ፤ ደኀውም ማኅበረ
ሰብ ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ አንድምታው ባይገባውም ካርዱን ለመግዛት አቅሙን ስለፈተነው ለዚህ መንገድ ሰናይ ምላሽ አልሰጠም ነበር፡፡
ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚሉ
ይህን ሕዝቡን የነቀነቀውን ጉዳይ ማርቲን ሲመለከት በውስጡ የነበሩትን ጥያቄዎች ሁሉ አፈንድቶ ወደ 95 የሚደርሱ የተቃውሞ ነጥቦችን
በገዳሙ በር ላይ ለጥፎ ተከታይ የሚሆንም በማግኘቱ የራሱን አስተምህሮ መናገር ጀመረ፤ ለመፈጸም ያስቸገረውን የጾምና የጸሎት ሕይወትንም
በዚሁ ለጥፎ ከስልጣነ ክህነትና ከምስጢራት ጋር ገደል የሚከት አስተምህሮዎችንም አፍልቋል፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገበት ምስጢር ግን
ሰማያዊ ካርዷ ብቻ ናት ማለት አይደለም ሌሎች ተጨማሪ በካቶሊካውያኑ ይፈጸሙ የነበሩ የምግባርና የክብረ ክህነት እጸጽ ለዚህ ሁሉ
እንደዳረገው ታሪኩ ግልጽ አድርጎ ያስረዳናል ከእነዚህም ውስጥ፡-
·
ሲሞናዊነት፡- ወይም ሲሞኒዝም በሐዋ
8፡18 ላይ የምናገኘው ሲሞን የተባለ ጠንቋይ የነበረ ሰው ሐዋርያቱ ጋር ቀርቦ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታና ጸጋን መሳደር በገንዘቡ
ለመግዛት ያሰበ ሰው ነው፤ አይሁዳውያንም በመቅደሱ ይፈጽሙት እደነበርም በወንጌል ላይ እንመለከታለን ይህንም አምላካችን እግዚአብሔር
ሲያስተምረን የወንበዴዎችና ሻጮች መናኸሪያ ያደረጉትን መቅደሱን ጥሎ ሳይሆን የሄደው ከመቅደሱ አውጥቶ አጽድቷቸዋል በወንጌል ትርጓሜም
ርግብ ይሸቱ የነበሩትን ሰዎች በርግብ የሚመሰለውን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታና አገልግሎት ለሚሸጡ ሰዎች እንደሚመሰል ይገልጻል፤ ዮሐ
2፡16 ሐዋርያው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ቤተ-ክርስቲያን ቅድስናና ክብር ሲፈልጽ በ1ጢሞ 3፡15 “በእግዚአብሔር ማደሪያ
ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን
ነው” ይለናል፤ በካቶሊካውያኑ ይስተዋል የነበረው ሲሞናዊነት በሉተር ተቃውሞ ላይ ነዳጅን የቸለሰ ድርጊት መሆኑ ይገለጻል፤ በዚያን
ዘመን የክህነትን ክብርና ጸጋ በገንዘብና በዝምድና መስጠቱ ተጧጡፎ ነበር፤ ይህን መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ በቤተክርስቲያን ውስጥ
ቢሆኑን በሃይማኖትና ምግባር ከመርከቧ ውጪ የሆኑ ብዙ ሰዎች በተለያዩ ዘመናት ከሁሉም የእምነት ጎራ ይገኛሉ ፤ በእኛም ሃገር እንዲሁ
በአሞሉ ጨው ምስጢረ ክህነትን በመሸጥ ወንጀልን ይሰሩ የነበሩ የዲያብሎስ ልጆች እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፤ በአሁኑም ጊዜ ከገቢያ
በቀላሉ በሚገኙ ነዋያቶቻችን በመሸለም በገንዘብ ቆብ በመጫን የምንፍቅና መርዛቸውን የሚወጉ በገንዘብ የገዙና የተገዙ ሰዎች እንዳሉ
እየተመለከትን ይገኛል፤ በዚህ ጊዜ ጠንቀቅ ማለትና ቅድስት ንጽሕት የሆነች ቤተክርስቲያናችንን በንቃት ልንጠብቅ ይገባል፡፡
·
የናጠጠ የካቶሊካውያን አስተዳደሮች
ኑሮ፡- በምንኩስና ወደ አስተዳደሩ
ስልጣን የገቡት የካቶሊካውያኑ እጅግ የተቀማጠለ በምድራዊ ሃብት ተሞሽሮ መኖር ሌላ በውስጥ ልብስ ላይ እንደሚደረብ ኩታ ሆኖለት
ነበር፤ ተቃውሞውን የሚያጠናክር ነጥብና በእንርሱም ላይ ጥላቻ እንዲያድርበት አድርጎታል፤ በመሆኑም በጠዋት 95ቱን ነጥቦች በገዳሙ
በር ላይ ለጥፎ ከገዳሙ ወጣ፡፡
የካቶሊካውያን ፓትርያርክ የተሰጠው የማይሳሳት፣ የማይዋሽ ፍጹም የሆነ የክርስቶስ እንደራሴ ነው የሚለውን ትምህርትም
ሲሳሳቱ ስለተመለከተም ምስጢረ ክህነትንና የክንነትን ቅብብሎሽ የቆረጠ ስል ምንፍቅና ላይ ጣለው፤ በዚህም ክርስቶስ ብቻ እንጂ ፓፑ
የክርስቶስን ቦታ ይዞ እንደራሴ መሆን አይችልም ሲል ክርስቶስ ብቻ አለ፤ እንዲሁም ላሰላቸው የጾምና የተጋድሎ ሕይወት የምግባር
ስራ በጸጋው ብቻ የሚል አስተምህሮን አፈለቀ፤ ይህ ማለት ግን አሁን ባለው የመናፍቃን አስተምህሮ መጠንና ቅርጽ ሉተር ያስቀመጠው
አልነበረም፤ ካልቪን የተባለው የምንፍቅና አቀንቃኝ በተነሳም ጊዜ እኒህን አስተሳሰቦች እጅግ አስፍቷቸው አዋልድ መጽሐፍት፣ ቅዱሳን፣
ምግባር፣ ለቅዱሳን ምስጋና እንደማይገባ በማስተማር የምንፍቅናውን አድማስ አስፍቶታል፡፡
ለምን ይሆን ማርቲንን ክርስቶስ ብቻና በጸጋው ብቻ ያስባለው ስንል ሁለት ዐብይ ምክንያቶችን ተመልክተናል በነጥብ
ሲቀመጡ
·
የክርስቶስ እንደራሴ የሚባሉት የካቶሊክ የመጨረሻው የስልጣን እርከን ላይ ያሉት ፖፕ ትላልቅ ስህተቶችን እያዩ በመፍቀዳቸውና
እጸጽና ስህተቶችን በመመልከቱ ለብቻው ክርስቶስ ብቻ ሊል ችሏል፤ በዚህ የተነሳ እርሾ ግን የኋላ የኋላ ቅዱሳንም መቀበል ላይ ምንፍቅናን
አምጥቷል፡፡
o
1ጵጥ 2፡13 “ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፡፡”
o
·
በሁለተኛ ደረጃ በገዳም ያለችው የምግባር ሕይወት ክብደት ራስን በድንግልና ገዝቶ መኖር ከባድ መሆኑን በአመክሮ ጊዜው
ተመልክቶ ምርጫውን ከማስተካከል ይልቅ በመግባቱ አቅጣጫውን ለመቀየር የድንግልና የምነና ሕይወት አላስፈላጊ ነው ሊል ችሏል በዚያው
ገዳም የነበረችውንም ካትሪና የተባለች ሴት አግብቶ በጸጋው ብቻ ይዳናል እንጂ ተጋድሎ አያስፈልግም ብሏል፡፡
o
ማቴ 10፡38 “መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም”
o
ሮሜ 8፡7 “ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፡፡”
·
ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ያለው የሰማያዊ ካርድ ሽያጭ መንግሥተ ሰማያት ያስገባል የሚለው መጽሐፍ ቅዱስንና ስርዓተ ቤተክርስቲያንን
መሰረት ያላደረገ ድርጊት የሚጠቀስ ነው፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን
አስተምህሮ ስንመለከተው ምንም እንኳን በተፈጸሙት ነገሮች ቢመረርም ማርቲን የፈጸመው ድርጊት ከድጡ ወደ ማጡ የሚሰኝ እንደሆነ እንመለከታለን፤
እውነትንና የቀደመችውን ትክክለኛዋን መንገድ ከመመልከት ይልቅ ለሥጋው አድልቶ ለዓለማዊ ኑሮ የሚመቸውን አመለካከተት ይዟል፡፡
ሉተር
ሊያደርገው የሚገባው አዲስ መሰረትን በራሱ ከመቀየስ ይልቅ ቆም ብሎ ወደ ኋላ የቀደመችውን የአባቶቹን መንገድ ቢመለከት መልካም
ነበር የሚል ሃሳብ አለን፤ ለምን ቢባል እርሱ ያያቸው ችግሮችና የመሠረተ ሃይማኖት እጸጽ የሌለባት ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፍጽምት
ሆና የተሰጠች ሃይማኖች ነበረችና፤ ይሁ 1፡2 ፤ ኤር 6፡16 “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱንም
የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ፡፡”
ምሳ 22፡28 “የቀደመውን አባቶች ያስቀመጡትን
የድነበር ምልክት አታጥፋ” እንደተባለው ምንም እንኳን ከድንበሩ ቢወጣም እንደገና ጭልጥ ብሎ መጥፋት እጣው ሆኗል፡፡
እኛ ግን
ወንድሞቼ እኛ ግን በንጽሕት እናት ቤተ-ክርስቲያናችን እንጽና፤ የምንመለከታቸውን በጎም ይሁን ክፉ ነገሮች በማለፍ ካልሆነ ደልዳላና
የተመቻቸ የአገልግሎት ብቻ መስክ አንጠብቅ፤ በቀራንዮ ጌታችን አለ እመቤታችን ከመስቀሉ ስር ትታያለች የፍቅሩ ሐዋርያ ዮሐንስም
አለ ከቅዱሳን አንስት አርአያ የሚሆኑን ይልቁንም ሳትፈራ አምላኳን የወደደች መግደላዊት ማርያምን እናገኛልን፤ ከመስቀሉ ላይና ከመስቀሉ
ስር ዓይናችንን እልፍ ስናደርግ ጆሮአችንንም ጌታችን ስለ ድኅነታችን ይናገረው ከነበረው ቃል ከመስማት ስናርፍ የሚሰማው የአይሁዳውያን
ስድብና የሮማውያንን ጫጫታ ነው፤ አይናችንም ዙሪያውን ካማተረ ቁማርተኛ፤ ልብስን ገፈው የሚወስዱ ወንበዴዎችን ልበ ደንዳኖች አይሁዳውያንን
ነው የምንመለከተው፤ ዓይናችን ከመስቀሉ ይሁን፡፡
እንደ
ሐዋርያው “በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት
በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ በክፉ ወሬና
በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፡፡” ልንል ይገባናል 2ቆሮ 6፡5-8፡፡
ይልቁንም
የጸኑትን የእግዚአብሔር ቅዱሳን እናስብ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን
አስቡ፡፡” ዕብ 12፡3
1ኛ) እምነት ብቻ
እምነትን
ስንመለከት ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችን የተመሰገኑበት በልቦናቸው በዓይነ ሥጋ የማይታየውን ያዩበት ረቂቅ መነጽር ነው፤ ያለ እምነትም
እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ዕብ 11፡6፡፡ ነገር ግን የምግባርንም ሁሉ ቦታ ወስዶ እምነት ብቻ ማለት አንችልም ተገቢም አይሆንም
እምነት ያለምግባር ምውት ነውና፤ “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።”ያዕ 2፡27 ቀጠል አድርጎም አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ
“በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን?” ብሎ አባቶቻችንን ያመላክተናል ስለሆነም እምነት ፍጻሜዋን የምታገኘውና የምትመሰገነው
ከምግባር ጋር አብራ መንፈሳዊ ፍሬዎች ባሏት ጥበብ ስትፈተል ነው፡፡
ይልቁንም
እምነት ብቻ በቂ ነው ለሚሉ ሰዎች ከእምነትም በላይና ከእምነት በኋላ ሊሰሩ ስለሚገባ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፤ ለምሳሌ
ገላ 5፡6 ላይ ከፍቅር ጋር አብሮ የሚሰራ እምነት ይጠቅማል ብሎ ለብቻው እርቃኑን ከማቆም ይልቅ የሕግ ሁሉ ፍቃሜ ከሆነችው ከፍቅር
ጋር ደምሯታል፤ እንዲያውም ከአምስቱ ብቻዎች ዝርዝር ስፍራ ያላገኘችው ፍቅር ከሁሉ እንደምትበልጥ በ1ቆሮ 13፡13 “እምነት ተስፋ
ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው፡፡” ብሎ ያስቀምጥልናል፡፡
ሰው በእምነቱ
ብቻ ሳይሆን ከስራው የተነሳ ይኮነናል እንዲሁም ከስራውና ከምግባሩ የተነሳ ይጸድቃል እንጂ እምነት ስላለ ብቻ መንግስተ ሰማያት
አትወረስም ማቴ 12፡37፤ ለዚህ ነው ዮሐ 3፡18 “በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ
ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል፡፡” ይላልና እምነት የሌለው ሰው እዚሁ በምድር ይፈረድበታል እምነት ያለው ደግሞ ለሁለተኛ የምግባር
ፈተና በሰማይ ይቀርባል፤ እንደ ምሳሌ እንውሰድና አሁን
በመጣው የትምህርት ሂደት ደረጃ አንድን በትምህርት ቤቱ ጥሩ ውጤት አምጥቶ ያላለፈ ሰው ለሚቀጥለው COC ይቀመጣል እንዴ? COC የምንለው ፈተና ብዙው የተግባር
እንደሆነ ይነገራል፤ በሰማይም ያለው ፈተና ተርቤ አብልታችሁኛል ተጠምቼስ አጠጥታችሁኛል ታርዤ አልብሳችሁኛል የሚልና የመሳሰሉት
የምግባር ጥያቄ ነው በምድር የእምነት ፈተናን ሳያልፍ ለተግባሩ ፈተና ሊሰለፍ አይችልም፡፡
ምጽዋት፡-
ከመልካም
ምግባራት አንዷ እንደ ምሳሌ ምጽዋት መሆኗ ይታወቃል፤ ስለ ምጽዋት እግዚአብሔር አምላካችን እንዳስተማረን ሉቃ 6፡20 “ነገር ግን
ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፡፡” እንዲሁም ስጡ ድኅነትና ምሕረትም
ይሰጣችኋልና ይላል፤ ስለዚህ እነዚህን የመሰሉ የመንግሥተ ሰማትን በር የሚከፍቱ ሃብታተ ምግባር ከወዴት ደረሱ ያሰኛል ይህ አስተምህሮ፡፡
ይልቁንም እኛ የተዋሕዶ ልጆች አምላካችንና መድኃኒታችንን አርአያነት ተከትለን በእምነትና በምግባር
እንጸናለን “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው” ተብሎ በኤማሁስ የነበሩት መንገደኖች ለጌታችን እንደመሰከሩለት ሉቃ 24፡19፡፡
በመጨረሻ መናፍቃኑ ገለባነው ብለው የሚያስቡትን አስተምህሮታቸውን ሁሉ ከገለባ የቀለለ ያደረገባቸውን
የያዕቆብን መልእክት ሁለተኛውን ምዕራፍ ስንመለከት፤
“ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ
የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት
ምግብንም ቢያጡ ከእናንተ አንዱም። በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል?
እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፤ አንተ ከንቱ ሰው፥
እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን፡፡” ያዕ 2፡14-20 በማለት ሌላ ጥቅስ የማያሻ የማያዳግም መልስ የሰጠናል::
2ኛ) በጸጋ ብቻ
የጥንት
ቤተሰቦቻችን አዳምና ሔዋን ከበሉት አምላክነትን የመሻትና ሕጉን የመተላለፍ ታላቅ በደል እንደምን ዳንን ብንል ከረጅሙ ተራራ ያንን
ትልቅ ቋጥኝ ምንም ሳይፈነቅለው ልክ ንጉሡ ናቡ ከደነጾር እንዳየው ሕልም ትርጓሜና ፍች አምላካችን ፍቅር ስቦት ማንም ሳያስገድደው
ለልጆቹ ስላለው ፍቅር እንደመጣ አምላካችንም እንዲሁ ፍቅሩ አስገድዶት
መጥቶ አድኖናል፤ የመናፍቃን ስህተት ማለት ሙሉ ግድፈት ወይም ሙሉ ውሸት ብቻ ማለት ሳይሆን ያልተሟላ መረጃና ሃሳብም ነው:: ብዙውን
ጊዜ ጥቅስ እንኳን ፈጽመው እስከ ሃሳቡ ፍጻሜ ሳያነቡ ነው የሚስቱት፤ ሰይጣንም ግማሹን እውነት ወስዶ ከመርዙ ክህደት ጋር ቀይጦ
አስመስሎ ነው የሚያቀርበው፤ ቢያንስ እንኳ ከላይ እንደ ልብስ፣ እንደ ለምድ የሚሸፍነው እውነት አያጣም የየዋሃንን ልብ ለማስካድ፡፡
መጽሐፍ
በጸጋ ድናችኋል ሲል አምላካችን ምንም ሳንከፍልበት ከእኛ ምንም ሳይጠብቅ እንዲሁ ስለወደደን ሥጋችንን ነስቶ መጥቶ ከዚያ ከጥንቱ
በደል አድኖናል ማለት ነው፤ ይህ ማለት ግን ለወደፊት ምግባርና ከኃጥያት ርቆ መኖር እንዲሁም ተጋድሎ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ድነናልና እንዳሻን ለሚሉ የተጋባ መልካም
መልስ በመልእክቱ ይሰጣል ሮሜ 2:4 “ወይስ
የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?” በማለት የንስሃ ሕይወት ሊኖር እንደሚገባ ነግሮናል::
እራሳቸው
መናፍቃኑ በጸጋ ብቻ ብለው ከሚያነሱት ጥቅስ ብንነሳ ዝቅ ብለን ስናነብ መልካም ስራን ለመስራትና በምግባር ለመመላለስ በእግዚአብሔር
እንደተፈጠርን ያብራራልናል፡፡
ኤፌ
2፡8 “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ . .” ካለ በኋላ “እኛ
ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በኢየሱስ ክርስቶስ
ተፈጠርን።” ይላል ስለዚህ የጠፈጠርነው መልካም ምግባራትን እየሰራን
እንመላለስ ዘንድ ነው፤ መመላለስ
ማለት ድርጊትን ምግባርን ይገልጻልና። በመስቀሉ ላይ የተፈጸመው ድኅነቱ ግን እንደ እኛ ስራ ሳይሆን እንደ
ቸርነቱ ተፈጽሟል፤ በቅዳሴውም መካከል እኛም “አምላካችን ሆይ እንደ ቸርነትህ እንጂ እንደ በደላችን አይሁን” እንላለን አባታችን ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ መዝ 24:7 “የልጅነቴን
ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ::” እንላለን እንጂ እንደ ስራዬ ክፈለን ብለን በትእቢት
አንናገርም የመናፍቃኑ የጸጋ ብቻ አስተምህሮ ግን አስቀድመንም እንዳየነው ካነሳነው ሃሳብ ጋር የሚቃረንና መንገዱም ለየቅል ነው፡፡
|
ይህንንም
ሃሳባቸውን ለማጠናከር በመስቀሉ ላይ ሳለ በንስሃው በምግባሩ የተመሰከረለትን ፈያታዊ ዘየማንን እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ፤ እርሱ የዳነው
እንዲሁ አይደል ይላሉ፤ አስተውለን ግን ስንመለከት ምድር ላይ ስንመላለስ ብዙ ዓመት ከከረምነው ሰዎች ይልቅ ፈያታዊ ዘየማን በጥቂት ሰዓት ውስጥ ብዙ መንፈሳዊ ነገሮችን ሲፈጽም እናያለን፡፡ ከተፈጥሮ
ሲማር፣ ሲጸጸት፣ ሃጥያቱን ሲናዘዝ፣ ለጌታችን እርሱ ንጹሕ ነው ምንም በደል የለበትም ብሎ እንደ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ
ሲመሰክር እናያለን፡፡
(ማጣቀሻ፡-
በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ የሚለውን በማሕበረ ቅዱሳን መልቲሚዲያ ድሕረ ገጽ የሚገኘውን ትምህርተ ወንጌል ይመልከቱ ‹በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ›)
ፈያታዊ
ዘየማን ፍጹም የክርስትና የምግባር ግብሮችን ከፊሉን በምሥጢር ሌሎቹን ደግሞ በገሃድ
ፈጽሟል፡፡
ፈያታዊ
ዘየማን (ጥጦስ) የፈጸማቸው ተግባራት
v ጥምቀትን
ተጠምቋል
v ማኅተሙን
(ሥጋወ ደሙን) ይዟል
v ሰማዕት
ምስክር ሆኗል፤ ሰመዐት ማለት ምስክር ማለት ነው፡፡
v ንስሃ
ገብቷል ተጸጸቷል
v ታላቅ
እምነትን አሳይቷል መንግሥተ ሰማያትንና ዳግም ምጽአቱን አምኟል
v ጸሎት
ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነውና ጸልያል
v ጓደኛውን
ቢመለስ እንኳ ብሎ መክሯል (ወንጌልን አስተምሯል)
ድኅነት ምን
ማለት ነው?
ድኅነት ስንል ስለ 3ቱ የድሕነት ዓይነቶች ማንሳቱ ተገቢ ነው፤
1. የታችን
እኛን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የዓለም ሕዝብ ያዳነበት ድኅነት፤ የዚህ ድኅነት ተካፋዮች ሁሉም የአዳም ልጆች ናቸው፡፡
2. ከበሽታ
ከተለያዩ ደዌ መዳን ይህ ለታመመ ሲሆን እግዚአብሔር በተለያዩ ምክንያተ ድኅነቶችን በመጠቀም ያድናል፡፡
3. መንግሥተ
ሰማያትን መውረስ ድኅነት ነው፤ ይህ ድኅነት በእምነት በመኖር በምግባር በመላለስ ሥጋውን በመብላት ደሙን በመጠጣት ትፈጸማለች፤
“ሥጋዬን የማይበላ ደሜን የማይጠጣ የዘለዓለም ሕይወት የለውም፡፡” የተባለው ለዚህ ዓይነቱ ድኅነት ነው፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ተብሎም
የተነገረለት፤ የክርስትናን የምግባር መንገድ ሚጀምሩበት የድኅነትና ምስጢራት መግቢያ በር ጥምቀትም የተነገረለት ነው፡፡ መንግሥተ
ሰማያትን ለመውረስ ብዙ እርካብና እርከኖችን በሎዛ ያዕቆብ ተኝቶ እንደተመለከተው ሕልም ተረግጦ ማለፍን ይጠይቃል፡፡
የመሰላሉ ምስጢር ከጎንና ከጎን ያለው የሐዲስና የብሉይ ኪዳን ምሳሌ፤ እላዩ
ላይ የተደረደሩት ደግሞ እርካቦች የብዙ ምግባራትና ትሩፋት እንዲሁም የእምነትና የሥርዓት ምሳሌ ናቸው፤ በላዩ ይወጡና ይወርዱ የነበሩ
መላዕክት በተዘረዘሩት ሁሉ የመንፈሳዊነት ፍሬዎች ላይ የተመላለሱትን ቅዱሳን አባቶች ምሳሌዎች ናቸው፡፡
3ኛ) መጽሐፍ ብቻ
የዚህ
ጽንሰ ሃሳብ ዋናው ቅሉ መጽሐፍትን ብቻ ማለት ሳይሆን ለራሳቸው ልክ አድርገው የሰፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር ብዛት ልክ ብቻ
ለማለት ነው፤ ያልፈለጉትን አውጥተው የተመቻቸውን አስቀርተው በዚህ ብቻ እንመራበታለን ሚሏቸው በቁጥር ሲገልጹት 66 የሚሏቻ በአስተምህሮ
ግን ምንም መጽሐፍትን አልተቀበሉም የሚያስብሉትን ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ከጥንት አንስቶ በብዙ
ኅብረ አምሳል ተናገረ እንጂ በጥቂት ነገር ብቻ ለዛውም በቁንጽል መጽሐፍ ብቻ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ሃሳብ መገደብ ትልቅ ስህተትና
ሞኝነት ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን የላከውን መልእክት ሲጀምር “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ
ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ.”. ካለ በኋላ አሁን ግን በግልጽ በአካላዊ ቃል በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ
እንዳስተማረ ተናግሯል፤ ዕብ1 ፡1፡፡
መጽሐፍ
ቅዱስ በትንሹ አውቀን ብዙ እንድንሰራ ተጻፈልን እንጂ ራሳችንን አጥረት ብቻ እንድንቀመጥ የተቀመጠ አጥር ክልል አይደለም፤ መጽሐፍ
ቅዱስ በውኃ አቅጥነው አብዝተው እንደሚጠቱት የዱቄት ጭማቂ ያለ የሚመሰጠር የሚብራራ ብዙ ማጣቀሻን የሚስቡበት፤ እርሱ እንደ በሬ
ሆኖ ጥበበኛ በላች የሚፈልግ በኋላ በሊቃውንት በተለያየ መልኩ በየዓይነቱ የሚሰራ ምግብ ዓይነት ነው በምሳሌ ስንገልጸው፡፡
እንዲሁም
ደግሞ ጌታችንም ሐዋርያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፉ ብዙ ነገሮችን እንዳደረጉ ማወቅ ይገባል፤ ዮሐ 20፡30 “ኢየሱስም በዚህ
መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፡፡” ተብሏልና፡፡
ትውፊት
ትውፊት
ማለት በግዕዙ አወፈየ አቀበለ ካለው ግስ የወጣና መቀባበል፣ ቀብብሎሽ እንደማለት ነው፤ በግሪኩ “ፓራዶሊስ” ይለዋል ትርጉሙም ምንም
ይዞታውን ሳይለቅ በአድ ነገር ሳይጨመርበትና ያለውን ሳይቀንሱ ማቀበል የሚል ትርጓሜ ሲኖረው፤ በዕብራይስጡ ደግሞ “ማሳር / ቁቡል”
መረከብና ማቀበል የሚል ትርጓሜ አለው፡፡
·
ሃይማኖት በትውፊት
ለቅዱሳን ተሰጥታ እኛ የተረከብናት ነች፡፡
o
ይሁ
1፡3
“ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡”
·
1ቆሮ 11፡23 “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፡፡”
ብሎ ሐዋርያትም ከጌታችን ተቀበሉትን ትውፊት እንዳቀበሉን ይናገራል፤ እንዲሁም “በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን
ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ፡፡” ብሎ የሐያቱን ወግና ስርዓት መያዝ ተገቢ መሆኑን ይናገራል፡፡
·
ሐዋርያት ያስተማሩትና የጻፉት በጽሁፍ የተረከቡትን ሳይሆን በዓይናቸው ዓይተው
በእጃቸው ዳሰው ያረጋገጡትን ነው፤ 1ዮሐ 1፡1 “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን
የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፡፡”
ወንጌል
ሲጻፍ በሁለቱ ሐዋርያትና በሁለቱ አርድዕት መጻፉ ስለ ወንጌል ክብርና ስለ ተረካቢዎቹ ስለ አርድእቱ ክብር ነው፤ ሐዋርያቱን መስለው
አክለው ተገኝተዋልና ሃይማኖትን ተቀብለው አቀብለዋልና፡፡
መጽሐፍ
ቅዱስንም ያገኘነው በትውፊት ነው፤ የተለያዩትን በአንድ ሰብስበው ምዕራፍና ቁጥር ሰጥተው የጸሐፊዎቹን ስም አድርገው አስቀምጠው፣
በቀኖና ወስነው ያስረከቡን ቀደምት አባቶቻችን ናቸው፡፡
ይልቁንም
በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተጻፉ ብዙ ነገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን፤ “እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው
አልወድም፥ ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ” 2ዮሐ 1፡12 ይህንን
ቃል በምን እናገኘው ይሆን; በትውፊት በሐዋርያት ስርዓትና ቀኖና አይደለምን;
አባታችን ቅዱስ ጳውሎስ 1ቆሮ 11፡34 “የቀረውንም
ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ፡፡” እንዳለ፡፡
ሐዋርያቱም
በቃል ብቻ ያስተማሩትን ብቻ ሳይሆን ምግባራቸውንም እንድንከተል በመልዕክታቸው አስተምረውናል፤ 2ተሰ 2፡15 “ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ
ቁሙ፥ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ፡፡” እንዲሁም 2ተሰ 3፡6 “ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን
ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን፡፡”
በዋነኝነት
አዋልድ መጽሐፍትና ሌሎቹም እስከ አሁን ድረስ የሚጻፉ መንፈሳውያን መጽሐፍት እንደሚጠቅሙ በምሳሌም በንብብም ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመለከታለን፡፡
n በምሳሌ
ሉቃ 10፡30 ጀምሮ ባለው ታሪክ
ወንበዴዎች
የደበደቡትን ሰው ሳምራዊው ሰው በአህያው ጭኖ ከእንግዶች ማረፊያ ከወሰደው በኋላ ሁለት የወርቅ ሳንቲም ሰጥቶ ለአስታማሚው፤ ከዚህ
በላይ ቢያስወጣህ ስመለስ እከፍልሃለሁ ብሎታል፡፡ ሁለቱ ሳንቲም ሐዲስ ኪዳንና ብሉይ ኪዳን የእንግድነት ማረፊያ ይህች ምድር ቤቷ
ቤተ ክርስቲያን አስታማሚው መምህራንና ካህናት ዳግም ስመለስ መባሉ በዳግም ምጽአቱ ተጨማሪ ዋጋ ቢያስወጣህ የተባሉ ሌሎች ማስታመሚያ
ሚሆኑ መጽሐፍትን፣ ድርሳናትን ብታዘጋጅ ሲል፡፡
n በንባብ
2ጢሞ 3፡15 “ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን
አውቀሃል፤ የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና
ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል፡፡”
4ኛ) ክርስቶስ ብቻ
እንግዲህ
መናፍቃኑ አስቀድመን እንደተናገርነው ይልቁንም ሉተር በምድር ሲፈጸም ያየው የነበረውን በቤተክርስቲያን ሆነው ይፈጸሙ የነበሩትን
ክፉ ነገሮች በማየቱ፤ ይልቁንም የክርስቶስ እንደራሴ ተብሎ በሮማ መንበር ላይ የተቀመጠው ፓትርያርክ እንደተባለው ሆኖ ስላላገኘው
ተሰባሪን ሰው አይቶ ወድቋል፡፡ ምሳ 3፡5 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፡፡” ያለው እንዲሁ
እንዳንወድቅ ነው፤
ሮሜ
8፡30 “አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ
አከበራቸው፡፡”
ቅዱስ
የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቅዳሺ፣ በሱሩስት ቃዲህ፣ በዐረብና በግዕዝ ቅዱስ ይለዋል፤ ትርጓሜውም ክቡር፣ ንጹሕ፣ የተለየ፣ የከበረ
ልዩ ማለት ነው፡
አምላካችን
እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ ኢሣ 5፡16 “ቅዱስ ቅዱስ ቅደሱ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዳለ፡፡” የእርሱም ቅድስና የባሕሪው ነው፤
የባሕርይ ማለት ከማንም ያልተቀበለው ያልተሾመው ማለት ነው፡፡
የጸጋ
ቅድስናስ ምንድን ነው ብንል በባሕሪው ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የሚሰራ ሁሉ ከባሕሪው ተካፋይ ሆኖ ቅዱስ የሚሆን
ማለት ነው፤ እሳት በባሕሪው እንደሚያቃጥል የማያቃጥለው ብረት ወይም እንቸት ሲገባበት ደግሞ እንጀቱም የሚያቃጥል ብረቱም ግሎ የሚፋጅ
እንደሚሆን፤ ብረቱን ከእሳቱ ቢያርቁት ማቃጠል እንደሌለው ከእግዚአብሔር የተለየ ቅድስና የለም፡፡
ስለሆነም
ከእግዚአብሔር ጋር ያሉ ሁሉ ቅዱስ ይሆናሉ ብለን ከምናነሳቸው ውስት ቅዱሳን ነብያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ነዋያት፣
አድባራትና መካናት ሌሎቹም ይጠቀሳሉ፡፡ ስለሆነም ክርስቶስ ብቻ የሚሉት ሰዎች መጽሐፉን ቅዱስ ብለው እርሱን ብቻውን ማስቀመጥ አይችሉም፡፡
5ኛ) ምስጋና ለእግዚአብሔር ብቻ
ምስጋና
ለእግዚአብሔር ምግቡ ነው ይላሉ ሊቃውንት፤ ስለዚህ
ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል፤ ነገር ግን ብቻ የምትለው ቃል አሁን ቃሉን ወደ ሌላ ትርጓሜ የምትወስድ እርሾ ነች፤
ማቴ 16:6 “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” 1ቆሮ 5:6 “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን?”::
ይልቁንስ ምስጋና ለሚገባው ምስጋናን ስጡ ብሎ መጽሐፍ ያስተምረናል ሮሜ 13:7 “ለሁሉ
የሚገባውን አስረክቡ፤ . . ክብር
ለሚገባው ክብርን ስጡ” እኛ ኃጥአን አደለም ቅዱሳኑ እንኳን
መልካም ያደረጉትን ሲያመሰግኑ እንመለከታለን፤ 2ዮሐ 1:5 “እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ”
በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ በጣም የሚገርም ታሪክ አለ፤ አባታችን ቅዱስ ዳዊት በስደት ሳለ
የተፈጸመ 1ሳሙ 25 ላይ ሙሉ ታሪኩን ስንመለከት ናባል የተባለ ምናምንቴ ሰው ነበረ ይላል ዳዊትንም በመናቁ ሰራዊቱን አስከትቶ ሊያጠፋው በተነሳ ጊዜ የናባል ሚስት የሆነችው አቢጊያ ከመንገድ በጥበብ ጠብቃ
በከንቱ የሰው ነፍስ ከማጥፋት ስለታደገችው በሚገርም ቃል አመስግኗታል 1ሳሙ 25:33 “ወደ ደም
እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ” ብሎ እኛ መልክ ብለን ጸሎትን በምናደርስበት አይነት ሁኔታ አመስግኗታል፤ እዚህ ላይ የሚገርመው ግን የአቢጊያ አይምሮ የተመሰገነ
ይሁን ከተባለ ክፉ ሃሳብ ለቅጽበት እንኳን ያልጎበኘው የእመ አምላክ አእምሮ እንዴት አይመሰገን? እኛ ግን እንዲ እያልን ከፍጥረት
የከበረች እናታችንን እናመሰግናለን “ሰላም ለሕሊናኪ ሐልዮ ሠናያት ልማዱ፤ ወገቢረ ምሕረት ምፍቅዱ፣ ማርያም ድንግል ለዳዊት ወለተ
ወልዱ ንዝሕኒ በአዛብኪ ዘኢያትረከብ ዘም፥ ወበማየ ሕይወት ኅፅብኒ እምበረድ እጻዕዱ።” ትርጉም “እመቤቴ ማርያም ሆይ በጎ ነገር
ማሰብ ልማዱ ለሆነ ኅሊናሽ ሰላምታ ይገባል፥ ምሕረት ማድረግ የሁል ጊዜ ተግባሩ ነውና። ድንግል ሆይ ከዳዊት ባሕርይ የተገኘሽ የዳዊት
የልጅ ልጅ ነሽ፡ ከበደሌ እነጻ ዘንድ ምሳሌ በማይገኝለት በሐር መነሳንስ በሂሶጵ እርጭኝ በሕይወት ውኃም አጥበሽ ከበረዶ የነጻሁ
አድርጊኝ::”
ሌላው ነጥብ ደግሞ አንድ ኃጥእ በተመለሰ ጊዜ የሚሰማው የመላእክት ምስጋና ነው እንዲሁም መንግሥቱን
ለመውረስ የተገባች ነፍስ ከሆነች በደስታና በምስጋና ያሳርጓታል፤ ንጹሐኑ መላእክት ለእኛ ለኃጥአኑ መመለስ ደስ ተሰኝተው ተዘመሩ
እኛ ደግሞ በደስታ የተመሉትን የአእላፉን መላእክት ሕብረት የምንቀላቀል
እንዴት አናመሰግናቸው!:: ዕብ 12:22 “ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ
ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት::”
በአጠቃላይ ግን እግዚአብሔር የባሕሪ ገንዘቡ የሆኑትን ለወዳጆቹ በጸጋ እንዳደላቸው መገንዘብ
አለብን:: 2ጴጥ 1:2 - 4 “የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን
ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና
እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን::”
ከዚህ ያለፈውን በነገረ ቅዱሳን ትምህርት ላይ ለቅዱሳን የሚገባውን ክብር በሰፊው እናጋኛለንና
በዚህ ዙሪያ የተጻፉ መጽሐፍትን ብንመረምር የላቀ መልስ እናገኛለን::
ይቆየን . . .
ጻድቃንን በገዳም ሐዋርያትን በደም ያጸና
አምላካችን እኛንም በተዋህዶ ሃይማኖታችን ያጽናን!
No comments:
Post a Comment