በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
የጽሑፉ ዓላማው፡- ውጫዊ የሆነ መንፈሳዊነት ብቻ ደምቀን ውስጣችን ግን በመረረ ፍሬና ክፉ ምግባር የሆነብን ሰዎችን መምከር
ዶሮ
አራት መአዘን እንቁላል ጥላ አታውቅም በግ ፍየልን ወልዳ አታውቅም ሁሉን ስነ ፍጥረት እግዚአብሔር አምላካችን በሚመራቸው ሕግ ታዘው
ይመራሉ፤ የዛሬ 1000 ዓመት በፊቱ በሬ አሁንም በሬ ነው፤ አሁን ተነስቼ የምነቸውን ሳር ትቼ ስጋ በል ልሁን አላለም፤ የሰው
ልጅ ግን እንዳስቀመጡጥ የማይገኝ ዕቃ የተባለውን የማይሰማ አማጺ ነው፤ የተከሉበት በመገኘት ዛፍ እንኳን ይበልጠናል ተነቅሎ ሌላ
ቦታ አይሄድምና የእኛ የሰዎች ክፋት እግዚአብሔር እንኳን በሰው ልጅ ግብር እጅግ አዝኗል ቃላት ስላልተገኘለትም ለባሕሪው የማይስማማውን
ጸጸት እንኳን ተጸጸተ እስኪባል ድረስ ከተፈጥሮ ውጪ ሲከውን የሰው ልጅ ተገኝቷል፡፡
በአንድ
ወቅት አንዲት ላም ነበረች አሉ፤ ይህቺ ላም በለምለሙ መስክ ላይ ተሰማርታ እንደ ፈለገች እየቧረቀች ያሻትን ሳርና ቅጠል እየቀነጠበች
ትውል ነበር በጣም ደስተኛ ትመስላለች ስትታይ፤ ደግሞ ሌሎቹ ላሞችም ለእርሷ ልዩ አክብሮት ይሰጧታል፤ ነጭ ነቻ! የምታምር ነጭ ላም፣ በውበቷ እንደ እርሷ የተጠቀም የላም
ዘር የለም መቼም፤ ስትሔድ ለሳሩ እንኳን አታዝንለትም ዳግም አንገቷን ደፍታ የምትግጠው እንኳን እስክትመስል ድረስ አንገቷን እንደ
ዝንብ ማባረሪያ ጭራ እወዲያና እወዲህ እያደረገች ምንም ስራ ባይኖራት እንኳን ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ትሄዳለች፣ ተንጎራደዳለች፡፡
አይደርሱ
የለ ያ ቀን ደረሰ፡፡ የቱ? አትሉኝም መታለቢያዋ ነዋ፤ ለአቅመ ላምነት ደርሳለችና መሳያን ጥጃ አፍርታ እንገሩን ከአጠባች በኃላ ባለቤቶቹዋም
ከበለሳቸው ለምግብነት ፍሬን እንደሚጠብቁ ከእርሷም የሚጠጡትን ወተት ፈለጉ፤ የምታልበው ገረድ ከስር መደቀኛዋን ይዛ ጥጃዋን ከላሟ
ፊት ለፊት አስራ ስታበቃ የላሟን የወተት ምንጭ በእጆቹዋ ይዛ በጥበብ ወተቱን ጠራችው፤ አንድ ሁለት ሦስት ጊዜ ሷ . . ሷ .
. ሷ . . ካደረገች በኋላ ወደ እቃዋ ብትመለከት ያልጠበቀችውን የወተት አይነት ተመለከተች በአግራሞት ጎነበስ ካለችበት ቀናብላ
ደግማ ከወተቷ ጨመረችበት “ከዕቃው ነው? ወይስ. . ; አለች በአግርሞት በመጨረሻ ግን አረጋገጠች ጥጃው ለካ እንደዚህ ወተቷን
የተጸየፈውና የከሳው እንገር ነው ብሎ የጠባው ችግር ስለሆነ ነው! ከላይ የሚገርም ካባ አልብሶሽ ነበር ታዲያ የት አለ ዋናው ቁም ነገሩ፤ አለቻት
ላሚቷ ትሰማት ይመስል እያዋራቻት፤ መልስ ስላጣች በዝምታዋ ተናዳ ገረዷ ቀጠለች እኛ አንቺን የቁንጅና ውድድር ለማሳተፍ እኮ አይደለም
ቀን ከሌት እየለፋን የምንቀልብሽ አለቻት በንዴት፤ በዚህን ሰዓት ላሟ መልስ ብቻ አይደለም የሚመልስላት
እንኳን አጣች መቼስ ፋንድያ የሚዝቀው እንዳይከራከርላት እርሱ ለራሱ አላፈራ ብሎ ያስቸገረ የበለስ ዛፍ ስራ ጠምዶታል፤ አላቢ ገረዷ
በይ ለአሁን እሺ ለነገ ግን ይኼን ወተት ቀይረሽ እንዳገኝሽ አለቻት ለላሟ በማሰብ በተማጽኖ፤ ላሟ ጥሩ እድል ነበር የገኘችው ነገር
ግን ላሟ ይባስ ብላ፤ ይኼ ምንሆነና ነው የምቀይረው ከዚህ ቀደም የነበሩት ላሞች ማምጣት ያልቻሉትን ልዩና በጣዕሙ አዲስ ወተት
ስላቀረብኩ ነው፤ ብላ አንድ ቅንድቧን ወደ ተራራ አንዱን ደግሞ ወደ ጎተራው አመሳቅላ በቁጣ ተናገረቻት ይባስ ብላ የቀድሞውን ስርዓት
ናፋቂ ለውጥ ጠላት አይሁድ ባላ ሰደበቻት ላሟ ከየት እንደ ሰማችው እግዚር ይወቀው ግን አለቻት፤ አሁን አሁን ዲሽም እበረት ውስጥ
ሳይኖር አይቀርም መሰለኝ፡፡
ምናለበት ላሟ የነገሯትን ብትሰማ
ልጇን ያልሆነ ወተት አጥብታ ከምትጎዳው እኛም ከእርሷ ሳንጠቀም አብልተን አብልተን ከምንከስር ትክክለኛ ወተት ብትሰጥ .
. አልኩኝ ለራሴ፤ እውነት ላሟ ትቁር ሆና ወተቷ ነጭ ቢሆን ብዙዎች
በተጠቀሙ አልኩኝ አንዳንድ ከሌላ ከበረቱ ውጪ የተወለዱ ጥጃዎች የላሟን ልዩ ወተት አዲስ ነገር በሚል ፈሊጥ አብረዋት ሲከራከሩ
ሰምቻለሁ፡፡
አሁን አሁን የክርስቲያን ወገኖች
ከወተቱ ይልቅ ወደ ሌጦው እያዘነበልን የመጣንበት ከላይ ያማረ መሳይ ፍሬና ወተት ግን ሲፈለግበት ተራ ሰዎች የበዛንበት ዘመን ላይ
እገኛለን፤ ለምን ይሆን? ብዙ አስተማሪዎች ብቅ ብለዋል እናት ቤተ ክርስቲያናችንም ማኅጸንዋ ከመውለድ አልነጠፈምና በየዘርፉ አገልጋዮች
ፈርተዋል ሊመግቡን ሲመጡ ግን እንደ እሬት የመረረና ጣእም አልባ ወተት ያላቸው ተበራክተዋል፤ ግርማ ሞገስና አለባበሳቸው ብቻ አምሮ
ፍሬያቸውን እንደ ቀደምት አባቶቻችን ካላሳዩን ምንድን ነው ትርጉሙ; አበው አስቀድመው ዳዋ ለብሰው ጤዛ ልሰው ዋሻ ምሰው በዱር
በገደሉ እየተዘዋወሩ በሰው ዓይን ውስጥ የሚገባ ሰውነትና ልብስ እንኳን አልነበራቸውም ነገር ግን በጸጋ እግዚአብሔር የተቃኘ ትምህርታቸው
ዛሬም ድረስ ህያው ሆኖ ከነፍስ ደዌ ይፈውሰናል፡፡
እግዚአብሔር ሁሌም ልቡናችንን
ነው የሚያየው “ሰው
ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” ተብሎ ተጽፏልና 1ሳሙ 16፡7 እንዲሁም ከእኛ የሚፈልገው እንቅስቃሴያችንን፣ ግርማ ሞገሳችንን፣ በሳሙና አጥበን
የለበስነውን ልብሳችንን አይደለም “ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ” አለ እንጂ ምሳ 23፡26፤ ቅጠላችን አምሮ መራራ ፍሬን አናፍራ ከላሟ
ቆዳ ወተቷ ልጆችን እንደሚያሳድግ እንወቅ በሃይማኖት ያልጎለመሱ የቃሉን ወተት የሚመኙ አሉና ስለወተቱ እንጠንቀቅ፤ ላሟም ምንም
እንስሳ ብትሆንም የሚያስከብራትና ጌታዋ ቤት የሚያኖራት ወተቷና ሊያርስና ሊያገለግል የሚችል የፈረጠመ ኮርማ በሬ ማፍራት ስትችል
ነው፤ እኛም በጌታችን ቤት እየኖርን ቃሉን ተቀልበን ስንኖር ሁሌም ፍሬ ይጠበቅብናል የክርስትና ውጤቱ እግዚአብሔር እንዲከብርብን
አፍርተን መገኘት ነው፤ በውጭ መድመቅና መብረቅረቅ ገበያ ላይ ለሚያታልሉን ዕቃዎች እንኳን አልበጀምና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment