የቃሉ ተናጋሪ አጠራሩ ገና በታናሽነቱ ዘመን የነበረው፣ አግዚአብሔር እንደልቤ የሆነ የዕሴይ ልጅን አገኘሁ ብሎ የተናገረለት ቅዱሱ ዳዊት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ
ዳዊት ይህን ከላይ በርዕስነት ያነሳነውን ቃል የተናገረበት ዘወትር የማይዘነጋው አንድ ዓቢይ ምክንያት ነበረው ፡፡
የእግዚአብሔር ወዳጅ ቅዱሱ ዳዊት ገና ንጉሥ ሣይሆን የቀድሞው ንጉሥ ሳዖል ላይ በበደሉ የተነሣ የተፈጸመበት አንድ ነገር ያስታውስ
ነበር ይህም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከሳዖል መወሰድ ነበር፤ አስቀድሞ ሳዖል ለንግሥና ሳይበቃ በልጅነት ሳለ እንዲህ ተብሎ
ተነግሮለት ነበር “ቂስም ሳኦል የሚባል የተመረጠ መልካም ልጅ ነበረው፤ ከእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ይልቅ መልካም የሆነ ሰው
አልነበረም፡፡” 1ሳሙ 9፡2፤
ልጅ ሳለ ስለ ሳኦል የመልካምነት ዝና ሰዎች ሁሉም እንደሚያውቁት ሕዝበ እስራኤልም እንደሚያወራለት ከዚህ ጥቅስ መረዳት
እንችላለን፡፡ የሳኦልና የዳዊትን ነገር ስናነጻጽር ዳዊት ብላቴና ሳለ በሰዎች ዘንድ ግምት ያልተሰጠው እንዲያውም የተናቀ
እናቱና አባቱ እንኳን የተውት ሰው እንደነበር ነው፤ እርሱ ራሱ “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ።” መዝ
26፡10 ብሎ በመዝሙሩ ከትቧልና፤ እስራኤል ስለ ሳኦል መልካምነት ቢያወሩም መልካምነቱ ግን አህያ ጠባቂ ሳለና በድህነት ኑሮው
ሳለ ብቻ ነበር አብሮት የቆየው፤ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ንጉሥ ካላነገሥክልን ብለው ሲያስጨንቁት ራሳቸው የሚያውቁትን፣
ጅማሮው በእነርሱ ዘንድ መልካም የነበረውንና በጸባዩ መልካም እንደነበር መንደርተኛው የሚያወራለትን ሳኦልን ሾመላቸው፡፡ ልዑል
እግዚአብሔር ስለ ልባቸው ክፋትና ደንዳናነት ብሎ እንኳን ክፉ የሆነ ሰውን አላነገሠባቸውም፤ እርሱም ተቀብቶ የንግሥናውን በትረ
መንግሥት እንደጨበጠ ትህትናውና መልካምነቱ እዛው ከአህያዎቹ ማሰማሪያ ሜዳ ላይ ቀረ፤ በምትኩ ትዕቢት ገዛው፤ ሹመትን በአግባቡ
ካልተጠቀምንበት ሺ ሞት ይሆናል ይባላል፡፡
እውነት ነው! ሳኦል ከድፍረትም በላይ በሆነ ድፍረት ለእግዚአብሔር አልታዘዝም በማለቱ ታላቅ ሞት መጥቶበታል፤
እግዚአብሔርን መፍራት “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” መዝ 110፡10፣ ምሳ 9፡10 ብለው የተናገሩ ነገሥታት ዳዊትና ሰሎሞን በሕዝቡም በእግዚአብሔርም ዘንድ
ክብርንና ሞገስን እንዳገኙ እናውቃለን ንጉሡ ሳዖል ግን እግዚአብሔርን አልፈራም ካህኑና ነቢዩ ሳሙኤል የሚያቀርበውን መስዋእት
እንኳን በራሱ ፈቃድና ሥልጣን ሰዋ፤ በዚህ ድርጊቱ የገፋው ሳኦል የከፋው ድርጊቱ ደግሞ እግዚአብሔር የእስራኤልን ተቀናቃኝና
የዘወትር ጠላት የነበሩትንና ከግብጽ ምድር ወጥተው ወደ ርስት ሀገራቸው ከነዓን ሲጓዙ በጦር እየወጉ አደጋ እየጣሉ ይገድሏቸው
የነበሩትን፣ መንገድ እንኳን አንሰጥም ብለው ማኅበረ እስራኤልን ሌላ ረጅም መንገድ አስቀይረው ዮርዳኖስን ሁለት ጊዜ ተሻግረው
ሀገራቸው እንዲገቡ ያደረጉትን ፣ይህ አልበቃ ብሎ ሀገራቸው ከገቡ በኋላ እንኳን የሚዘሩት ማሳ ገና እየበቀለ ከሆነ እየነቀሉ
ለፍሬ የደረሰ እንደሆነ ደግሞ እሳት እየለቀቁ እጅግ በጣም ያስቸግሯቸው የነበሩ አማሌቃውያን የሚባሉ ነበሩ፤ታዲያ እግዚአብሔር
ለእነዚህ ለክፉ አድራጊዎቹ የእጃቸውን ሊከፍል ለእስራኤላውያንም እረፍትን የሚሰጥበት ጊዜ በደረሰ ጊዜ በሳኦል የንግሥና ዘመን
አማሌቃውያንን ያጠፋ ዘንድ በነቢዩ በሳሙኤል አማካኝነት እግዚአብሔር መልዕክት ላከበት ትዕዛዝንም አዘዘው፤ሳኦል ወደ
አማሌቃውያን ይዝመት ያጥፋቸውም ከእነርሱም አንዳች ሰው እንኳን እንዳይቀር ከአህዛብ ከብትም ንብረትም ከወርቅና ከሌላውም ቢሆን
አንዳች እንዳይነካ ሁሉንም እንዲየጠፋ አዘዘው፤ ዓለምን ድል ስንነሳ እግዚአብሔር ከእርሷ አንዳች እንድንወስድ አይፈቅድም ወደ
መንፈሳዊ ሕብረት ስንመጣ ሁሉን መናቅና መተው እንደሚገባ ተናገረን እንጂ፡፡ ሐዋርያቱንም ሲያስተምርና ሲያዛቸው ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአገልግሎታቸውና አሁን ላሉ አባቶቻችን መናንያንና መነኮሳት ምሳሌ ይሆን ዘንድ “ለመንገድም
ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ፡፡” ብሎ አዞአቸዋል “እኔ ከዓለም
እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምም ብሏል” ማር 17፡16፤ ዓለምን ድል ሲነሱ ዝሙቱን ትቶ ዘፈኑን አንጠልጥሎ መሆን የለበትም
ዓለምን ከነኮተቷ ኃጢአትንም ከነ ማደጎዋ መተው እንጂ፡፡
ሳኦል ግን የአህዛብን ንብረትና የሰቡ ከብቶችን ወሰደ እንዲሁም የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን ክብሬ ከፍ እንድትልልኝ ብሎ
ማርኮ ይዞ መጣ፤ ነብዩ ሳሙኤልም ከቤተ መንግሥቱ ሲደርስ ከብቶች ከጓሮ ታስረው ይጮሃሉ ወደ እልፍኙም ሲገባ ንጉሡን ማርኮ
እግዚአብሔር ኃይሉን አድሎ በሰጠው ድል ሳኦል በራሱ እንዳደረገው እየተደሰተ አገኘው በዚህም ጊዜ ሳሙኤል ስለምን
የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ቸል አልክ ብሎ ቢገስጸው፤ ሳኦል ልቡን አደንድኖ ይህን በማድረጌ ልክ አላደረኩምን ከብቶቹን
ለእግዚአብሔር መስዋእት ይሆኑ ዘንድ ማርኬ አመጣሁ አለ፤ ሳሙኤልም “መታዘዝ ከመስዋእት እግዚአብሔርን መስማትም የአውራ ስብን
ከማቅረብ ይሻላል አለው፡፡” 1ሳሙ 15፡22 የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ሳይሰሙ መስዋእቱን ማቅረብ ምንኛ ከንቱ ነው፤
እግዚአብሔር ከመስዋዕቱ ይልቅ ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ ይላልና፤
ዮሐ 14፡15፤ ብዙዎቻችንም ዕጣን፣ ጧፉን፣ ማስገበሪያውን፣ ዣንጥላውን የተለያየ መባውን እንጂ ራሳችንን መቼ እንደ
መስዋእቱ ለእግዚአብሔር አቀረብን በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደደው መስዋእት እንዲያውም እራሳችንን ንጹሕና ቅዱስ መስዋዕት
እድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ነው፤ “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ
ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ” ሮሜ 12፡1፡፡
ሳኦል ግን ለምርኮ ሳስቶ የእግዚአብሔርን ቃል ቸል አለ፤ እግዚአብሔርም ሳኦልን ንጉሥ እንዳይሆን ናቀው፤ ቅዱሱንም
መንፈሱን ከሳኦል ላይ ወሰደበት ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ይዞ መልካሙን የእሴይ ልጅ ዳዊትን እንዲቀባው አደረገ፤ ከሳኦልም
መንፈስ ቅዱስ ሲሸሽ መንፈሱ ይረበሽና ይጨነቅ ጀመር፤ የገዛ ልጁ ላይ ሳይቀር ጦር ይወረውር ነበር ሰላሙ ደፈረሰበት
የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ መተላለፍ እንዲህ ያደርጋልና፡፡ ሳኦል ከቃየል መማር ቢችል ለርኩስ መንፈስ ባልተጋለጠ ነበር ፤ቃየልን
በምድር ላይ ያቅበዘበዘው አትግደል የሚለውን የልቡና ሕግ ተላልፎ ወንድሙ አቤልን በመግደሉ ነው፤ የአቤል ደም ወደ መንበረ
ጸባኦት ደርሳ ስትጮህ በህሊናው ሲሰማ እረፍት አጣ ዘመኑን በሙሉ እንደትቀበዘበዘ ኖረ፤ መልካም ያደረገ ሰው ቢከሰስ ከግዞት
ቢጣል ሰላሙ አይደፈርስም ሐዋርያትን ሕግን ተላለፋችሁ ብለው ከእስር ቢያስገቡዋቸው እስር ቤቱን እንደ ቅኔ ማህሌት በምስጋናና
በደስታ የዘመሩበት ሕሊናቸው ከበደል ዕዳ ነጻ ስለነበረ ነው “ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ
ፍርሃት ይኖራልና” ምሳ 28፡1፤ የተከሰስንበትን ነገር ካልፈጸምነው ግን ምን ያስጨንቀን ይሆን? “በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ
የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?” 1ጴጥ 3፡13 ሐዋርያው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም በገላ 5፡18 “በመንፈስ ብትኖሩ ከሕግ
በታች አይደላችሁም” ብሏል፤ አዎን! መዳራት፣ ጣኦትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣
መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት ሕግ ከላይ ሆኖ ያስፈርድባቸዋል ከምድር ፍርድ ቢያመልጡ እንኳን
እውነተኛው ዳኛ እግዚአብሔር እኚህ ላይ ይፈርዳል፤ መንግሥት ሠማያዊትንም መውረስ አይችሉም፤ ነገር ግን ፍቅር አላችሁ ብሎ ማን
ይከሠናል? ደስታና ሰላም ይሰብካሉ ብሎ ማን ይቃወመናል? ትዕግስትና ቸርነት በጎነትንም ጠልቶ ማን ይህን ተው ይለናል? የዋህና
ራሳችንን የምንገዛ ብንሆን ለሁሉ መልካም አላደረግንምን? ጥሩውን ጠልተው ክፉውን የወደዱ እንደ አባቶቻችን የሰማእትነት ዘመን
የነበሩ ሰዎች ቢኖሩ እንኳን ከአምላካችን የተገባልን ቃል ኪዳን “ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን
ናችሁ።” የሚል ነው፤ እንዲሁም ስለሚሰጠን ሰላም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገልጽ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥
ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።” ዮሐ 14፡27 ብሎ በጦርና
በእሳት በእስር የማይታወክ ሰላሙን እንደሚሰጠን መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡
ቅዱስ ዳዊት ለሳዖል በገናን እየደረደረ ክፉን መንፈስ ከእርሱ ያርቅ ነበር ከጭንቀቱም ያሳርፈው ነበር፤ የእግዚአብሔር
መንፈስ ከሳኦል ርቋልና ክፉ መንፈስ ሳኦልን ያሰቃየው ነበር፤ ዳዊትም በየቀኑ ያደርግለት እንደነበረው በገናውን ሲደረድርለት
ሳኦል በእጁ የያዘውን ጦር መንፈሱ ጸንቶበት ዳዊትን ከግድግዳው ጋር ለማጣበቅ ይወረውርበት ነበር፤ ሳኦል ጅማሮው ያማረና
መልካም ሰው ቢሆንም ፍጻሜው በንስሃና በጸጸት ሳይደመድም ሞት ወሰደው፤ ዳዊትም በንግሥናው ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ እርሱም ከነገሠ
በኋላ በልጅነቱ በገናን ሲደረድር የነበረውን መንፈስ ቸል በማለት እግዚአብሔርን በደለ፤ የባሪያውን የኦሪዮንን ሚስት ቤርሳቤህን
አስነውሮ ኦሪዮንንም ኃጢአቱን የሚያሸፍን መስሎት አስገደለው፤ በዚህም እግዚአብሔር ተቆጣው ገሠጸውም በዚህ ጊዜ ነው መምህረ
ንስሓ የሆነ አባታችን ቅዱስ ዳዊትም በእንባ በልቅሶ ማቅን ለብሶ አመድ ነስንሶ በንስሐና በጸጸት መሪር እንባን አለቀሰ እንዲህ
እያለም ጸለየ እንደ “ስራዬ ሳይሆን እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ ከበደሌ ፈጽሞ
እጠበኝ ከኃጢያቴም አንጻኝ” አለ እንዲያውም አስቀድሞ በጎቹን ሲጠብቅ የነበረውን የዋህና በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ልብን ለመነ
“አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” ካለ በኋላ እንደ ሳኦል ለክፉ ጠላትና የአእምሮ ጭንቀት
እንዳይዳረግ “ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ” አለ መዝ 50፡1–11፡፡ ቅድስ ዳዊት
የእግዚአብሔር መንፈስ ከተወሰደበት ምን እንሚጠብቀው ከሳኦል ተምሯልና ከሁሉም ያሳዘነውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ምንም ቢበድል
እንዳይተወው ለመነ፡፡
እኛም ሁላችን ይህ ቅዱስ መንፈስ በ40 እና በ80 በጥምቀት ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ስንወለድ
የታተምንበት ነው፤ ነገር ግን ስንቶቻችን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ሳናሳዝን እንኖራለን? ቅዱሱ መንፈስ
አልተወሰደብንምን? ይህንን የምናውቀው ጣፋጩ ሲመረን፣ ከዚህ በፊት እንደ ሕጻን ልጅ እያስፈነደቀ ደስ የሚያሰኘን ነገር አሁን
ቁንጥጫ ሆኖ ካስለቀሰን፣ ሌት ተቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት እየገሠገስን ስናገለግል ያልደከመን ጽናታችን ተገፎ ስልቹና ዝንጉዎች
ስንሆን፣ የመንፈስ ዝለት ይዞን ከኃጢአት ለመራቅ የምናደርገው ጽኑ አቋማችን ሲሸረሸርና ላልቶ ከወደቅንበት መነሳት አቅቶን
ጭቃው ኋጢአት ላይ ስንንደባለል፤ አስቀድመን ትንሽ ሰው ብለን እንኳን ሳንንቅ እያከበርን ከወገባችን ዘንበል ብለን ሰላም
የምንል አሁን ቀሳውስት አባቶቻችንና ከፍተኛ ስልጣን ላይ ያሉትን ሊቀ ጳጳሳትን አይደለም እግዚአብሔርን እንኳን መፍራት
ተወስዶብን ቅዳሴና መቅደሱን ንቀን በወንጌሉም ቃል ስንቀልድበት ስንገኝ ያኔ ልንጠነቀቅ ይገባል ይህን የምናደርገው ቅዱሱ
የእግዚአብሔር መንፈስ ሲወሰድብን ነውና፡፡
በተወደደ ንስሐው ከሚደነቀው ጻድቅ አባታችን ቅዱስ ዳዊት ጋር ሆነን ከፊትህ አትጣለኝ ቅዱሱ መንፈስህንም ከእኔ
አትውሰድብኝ ልንል ይገባናል፤ ለመጾም ያለን ናፍቆት ከተለየንና ሦስት ቀን ሙሉ ስናከፍል በብርታት የምንቆይበት ጽናት ተገፈን
ለአንድ ቀን እራታችንን በስህተት ብንተው እስከሚነጋ መታገስ አቅቶን በሌሊት ሆዳችን ቀስቅሶ ካስበላን፤ ከቅዳሴው ስንመለስ
በነጠላችን እንዳልኮራንበት አሁን በሃይማኖታችን አፍረን ቅዱሱን መስቀል ከአንገታችን ላይ ከሸሸግን ከመዝሙር ይልቅ ዘፈኑ
አየማረከን ከመጣ ለቤዛነት የታተምንበት ቅዱሱ መንፈስ ርቆናል ማለት ነው፡፡ ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ ቅዱስ መንፈስህንም በውስጤ
አድስልኝ ብለን ልንጸልይ ይገባል፤ ቅዱስ ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር ሳለ መፈራትንና ሞገስን ሰጥቶት ነበር ሳኦል ግን ንጉሥ ሳለ
ኃይሉ ጦሩ ሁሉ ኖሮት ቅዱሱ መንፈስ ግን ከእርሱ ጋር ሲለይ ፈሪና ተቅበዝባዥ ሆኗል፤ ብላቴናውን ዳዊት እንኳን እጅግ ይፈራው
ነበር ሌሊቱን ሁሉ በስጋት በጭንቀት መንፈሱ ተረብሾበት ነበር፡፡
ወገኖቼ ዳዊትን ቅዱስ ያሰኘው ጅማሮው አይደለም ያማረ ፍጻሜው እንጂ! ስህተቱን መደበቁና መደባበሱ አይደለም የተወደደ
ንስሐው እንጂ! እግዚአብሔርም በጸጸት የተመለሰና የተሰበረ ልብን ፈጽሞ አይንቅም ንስሐን ይወዳልና እግዚአብሔር እንዲህ ይላል
“የወደቁ አይነሱምን? የሳተስ አይመለስምን? እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለ ምን ወደ ኋላው ይመለሳል?” ኤር
8፡4 ስለ እኛ የተነገረ ቃል ነው::
ይቆየን . . .
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይሕ ጽሑፍ በ2005 ዓ/ም መዝገበ ምሕረት መጽሔት ቁጥር ሦስት ላይ የተወሰደ ነው::