“በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን
የቀደመውን ዘመን አስቡ፡፡” ዕብ 10፡33
ሰው በነፍሱ ዝሎ እንዳይወድቅ ፈተናና መከራ ባጋጠሙት ጊዜና ፍጹም ዓለማዊ በሆነ የመንፈሳዊነት ብርድና ቆፈን ሲወድቅ የጸናበትን ዘመንና መንፈሳዊ ሲሳዮቹን ማሰብ አለበት፤
ይህንን ታላቅ ቃል የተናገረ አባታችን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው፤ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ በሚያጋጥመን ፈተናና መንፈሳዊ ተጋድሎ ውስጥ ጽናትን ማሰብ ታላቅ ስፍራ ስላለው ሐዋርያው ለዕብራውያን ምዕመናን በጻፈላቸው ክታቡ ላይ አብራርቶ ይህን ቃል ገልጾታል፤ “እንበለ ድካም ኢይትረከብ ጸጋ ፤ያለ ድካምና መከራ ጸጋን አትቀበልም” ነውና መንፈሳዊ ሰዎች እስከሆንን ድረስና በቅድስና
ሕይወት እስከተመራን ፈተና አይቀርም፤ ብርሃን የወጣበት ቀን እንዳለ እንዲሁ ማታም ይተካል፤ ጨለማ ላይ ሆነው ግን ማሰብ የሚገባው ድቅድቁን ጨለማ አይደለም ብርሃን እስኪመጣ መፍትሄ ፈልጎ ውቧን የማለዳ ፀሐይ መጠበቅ እንጂ፤ ይበልጡኑ ደግሞ መንፈሳዊውን ሰው ብዙ መከራና ፈተና የሚደርስበት ከእግዚአብሔር በራቀ ቁጥር ነው፤ እግዚአብሔርም ልጆቹ ስለሆንና ስለሚወደንም በተለያዩ ተግሳጾች ይቀጣናል፤ እንድንመለስም በተለያየ መንገድ ይመክረናል ሕዝበ እስራኤል በነበሩበት በኦሪቱ ዘመን አምልኮተ እግዚአብሔርን ይፈጽሙ የነበሩ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ከዓለም ላይ ብቸኛ ሀገር ስለነበሩ በተለያየ ዘመን ጠላትና ችግር ይነሳባቸው ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜ ይህም የሚሆነው ከአምልኮተ እግዚአብሔር ፈቀቅ ሲሉና እግዚአብሔርን ሲያስቆጡ ነበር፤ ሀገራችን ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያም በታሪኳ ይህን መሰል ተግሳጽ አስተናግዳለች፡፡ እንደሚታወቀው በታሪክ የነዮዲት መነሳትና የነግራኝ አህመድ ጥፋት ምንም እንኳን ቤተክርስቲያንን የማይወድ የጠላት ዲያብሎስ ፍላጻና መከራ ቢሆንም በዘመኑ ግን የተባረደው/የደከመው/ የምዕመኑ መንፈሳዊነት ሕይወት አስተዋጽኦ እንደነበረው የቤተክርስቲያን የታሪክ ምሁራን ያዘክራሉ፣ ስለሆነም ከጥፋት እንድንመለስ፣ ከድካምም እንድንበረታ ሁልጊዜም በመንፈሳዊነት እንድንተጋ አምላካችን ልጆች ከሆናችሁ ትቀጣላችሁ ይላልና ስናጠፋ እንቀጣለን ስንቀጣም “ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?” (ዕብ 12፡8) በማለት በቅጣቱ እንድንታገስም ይመክረናል፡፡
ሰው ምንም ቢሆን በመንፈሳዊነቱ የጸናበትና በተጋድሎ የበረታበት ወቅት አለው፤ በአንጻሩ ደግሞ ሥጋው በመንፈሱ ላይ ኃይላ ነፍሱን የሚጎዳበት የድካም መንፈሳዊነት ወቅትም አለ፡፡ አብዝቶ የጾመበት፣ አድባራትንና ገዳማትን በፍጹም ልቡ የጎበኘበት፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ቀን ከሌት የተጋበት፣ ጠዋት ለኪዳን ተሰዓት ለቅዳሴው የሮጠበት፣ ነጋ ለኪዳን መሸ ለቁርባን ብሎ የጸናበት ከልቡ ስለበደሉ ያነባበት፣ በምጽዋትና በአስራት ሕይወቱ የታመነበት፣ በአገልግሎት የተጋበት በጥቅሉ ወደ ሰማያዊ ርስት የሚያደርሱ የመሰላሉን የመንፈሳዊነት እርካቦችን እየረገጠ የወጣበት ደገኛ ዘመን አለው፤ ታዲያ ዘመን ሲያልፍ ክፉ ቀን እንደሚያልፍ ሁሉ አያምጣውና በጎ የነበሩ ዘመናትም የሚዘነጉበት ወቅት አለ፡፡ ለእግዚአብሔርና ለቤተ-ክርስቲያናችን በፍቅር እሳት የነደደ ልባችን ሲባረድ፣ ለሰው ልጆችና ለበጎቹ (ለምዕመናን) ያለን ርህራሄና ፍቅር ሲቀንስ፣ ራሳችንን ዘወር ብለን ልናየውና ልንመረምር ይገባል፤ መጽሐፉም “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፡፡” ይላልና (2ቆሮ 13፡5)
ሥጋዊ ድካምና ጽናት
አንዳንድ ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንደዘቀጥን ቁልቁል እንዳሽቆለቆልን እየተረዳን ባለንበት ሥጋዊ ወጥመድ እስር ይዞን የተጨነቅን እንኖራለን፤ ስለዚህም ነገር ስለእኛ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ቃል ጽፎልናል “በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም፤ የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ፡፡”(ሮሜ 7፡18-20) እንዲሁም ቅዱስ ያዕቆብ የሰው ልጅ በሥጋዊ ምኞቶቹ እንደሚፈተን ጽፎልናል “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?” እንዲል (ያዕ 4፡1)፡፡ በመሆኑም ይህ ሥጋዊ አሳብ በእግዚአብሔር አጋዥነት ድል ልንነሳው እንደምንችል ራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ለሐዋርያቱ በታነገራቸው የማጽናኛ ቃል ያስተምረናል፡፡ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ 16፡33)፡፡ በዚህ የተስፋ ቃል መሠረት እኛም ዓለምን ድል እንደምንነሳት በቅዱሱ መጽሐፍ ተጽፎልናል፤ በሌላ መልዕክቱም ንዋየ ሕሩይ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ የሞትን መውጊያ የኃጢአትን ኃይል በሞቱ ገድሎ በትንሳኤው ለእኛ ለምዕመናን ኃይሉን እንዳደለን በጻፈበት ክታቡ ላይ “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው . .” ካለ በኋላ ይህንንም የሞት መውጊያ ኃጢአት ድል ነስቶ እንዳሸነፈልን አብራርቶ ስለዚሁ ውለታው ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን “ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” ብሏል፤ በእግዚአብሔር ኃይል ኃይልን እናደርጋለን፤ በአሸናፊው እግዚአብሔር ጠላታችንን ዲያብሎስን እናሸንፋለን፣ ሁሉን ማድረግ እንደሚችል አምነን በእምነታችን ዓለምን እናሸንፋለን “ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው፡፡” ይላልና እኛም በጥምቀቱ ከእግዚአብሔር ተወልደናልና ይህ ቃል ስለ ጥሙቃኑ የተነገረ በልጅነት ጸጋ የሚገኘውን በረከት የሚያስገነዝብ ማጽናኛ ቃል ነው፤ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና” (1ዮሐ 5፡4)፡፡
ደካማነትን አለመገንዘብ
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በረግረግ ዳጥ ላይ በአሸዋ ምድር ላይ ቆመን በጽኑ ዓለት ላይ የቆምን ያህል የተሰማን ወደ ኋላ ዞር ብለን ያልተመለከትን ራሳችንን ያልመረመርን የት ቦታ እንደቆምን በውል ያልተረዳን ብዙዎች አለን፤ በእውነቱ ከሆነ ሊታዘንልን የሚገባው እንዲህ ላለነው ሰዎች ነው፤ ለምን ካሉ “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ፡፡” (1ቆሮ 10፡12) ይላልና፤ የንጉሡ ሳኦልን ምግባር ያከፋው ልቦናውን እንደ ድንጋይ ማጠንከሩ ነው፤ ምን አጠፋሁ ብሎ በድፍረት ማሰቡ ነበር፤ ሳኦል የእስራኤልን ጠላቶች አማሌቅን አጥፋ ተብሎ ታዞ ትዕዛዙን ሳያከበር መጥቶ እርሱ ግን “የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፤” ነበር ያለው(1ሳሙ 15፡20)፡፡ በእውነቱ የኃጢአቱ ክፉነት የበደሉ ብዛት የታየውና ለንስሓ ራሱን ያዘጋጀ ሰው ብፁዕ ነው! ቁጥሩ ከሦስት መቶው ሊቃውንት የሆነው የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ እግዚአብሔርን ባነጋገረበት ጸሎቱ ላይ “ስለ ምን ስለ ኃጢአትህ አታዝንም ትለኝ እንደሆን ጻድቃን ወደ ቁርባን በሚሄዱበት ጊዜ የሚዘጋጁበት የልብ ጸጸትና ኃዘን የለኝም” ዳግመኛም እንዲህም እያለ ይለምናል “ጌታ ሆይ ለሚመለሱት የምትሰጣትን እንዲህ ያለችይቱን ንስሓ ስጠኝ፡፡” “ለኃጢአቴ ሥርየት ስለሠራህልኝ ጥምቀቴ ይቅር በለኝ፤ ኃጢአታችን ሊሠረይበት እንበላው ዘንድ ስለሰጠኸኝ ስለ አምላካዊ ሥጋህ ይቅር በለኝ፡፡” እኛም ከአባታችን ጋር ሆነን እንዲህ ብለን ልንለምን ይገባል፡፡
የማይተወን የማይጠላንም ለጥቅማችንም የሚቀጣን አምላካችን እግዚአብሔር አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ”ይለናል (ሕዝ 36፡26)፡፡ ስለሆነም ደንዳና ልባችንን በቅድሚያ አስወግደል የቀደመውን መልካሙን ሕይወታችንን አስበን ወደ አምላካችን እንቀርብ ዘንድ በንስሓ ተመልሰን ከጠባቂያችንና ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር ትዕዛዙንና ሕጉን ጠብቀን ልንኖር ይገባናል፤ ለዚህም አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፤ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት፣ የመላእክት ፈጣን ተራዳዒነት አይለየን፡፡
አሜን!