በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“ኢፈለጠ ወኢሌለየ አልቦ አይሁዳዊ ወአልቦ አረማዊ ኩሉ ዘየአምን ወጸዉዐ ስማ ማርያም
ዉእቱ ይድኀን ወይረክብ ሕይወተ?” መጽሐፈ ዚቅ
አንድ ቅዱስ አባት ማርያም ፊደል ናት አለ፤ ለምን
ፊደል መማሪያ እንደ ሆነ እኛም በእርሷ ነገረ መለኮትን፣ ምስጢረ
ተዋህዶን ተምረንባታል አውቀንባታል፤ አምላክ አስቀድሞ በሠማይ በልዕልና ሲኖር ተገልጾ አንድስ እንኳን ሠው ያየው አልነበረም አንድ
ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ተረከው እንጂ፤ ይህን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች ደግሞ ማን ናት? እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ናት እርሷ ከሴቶች ሁሉ ትለያለች ለምን የነፍሳችን መዳኛ የሆነውን ለነፍሳችን ረሃብ እውነተኛ ምግባችን፣ ለጥማችን ዘለዓለም የማንጠማበትን
(ፍቅር፣ ክብር፣ ውዳሴ፣ አምልኮ ለእርሱ ይሁንና) ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችልን፤ እመቤታችንን የወደድናትም ያወቅናትም ከመልዐኩ
ብስራት ፤ከጌታችንም ሰው የሆነባት ቅጽበት በኋላ ነው፤ በእግዚአብሔር ሕሊና ግን ትታሰብ ነበር፤ ለነገሩ የአምላክ እናት አይደለችም
እኛም በእርሱ ስለታሰብን የሚያስደንቅ አይደለም፤ እርሷ ግን ለድሕነት በልዩ ሁኔታ ትታሰብ ነበር፡፡
ለእኛ አምላክ ማለት ምን ማለት ነው? ኢየሱስ
ክርስቶስ ማን ነው? የእርሱን ክብር ከተረዳን የእመቤታችንን ክብር ማየት ቀላል ነው፤ የጌታችን የማዳኑ ስራን
ከተረዳን እንሱ የማዳኑን ስራ ሲፈጽም ከውልደቱ እስከ ስቅለቱ የአዲስ ኪዳንን ሰማዕትነት ከሐዋርያትም ከማንም ክርስቲያኖች በፊት
ሰይፍ በአንገቷ ያይደለ በልቧ ውስጥ አልፎ በስንት መከራና ተጋድሎ ያሳለፈች ድንቅ እናታችን እንረዳታለን እናውቃታለን፤ ወዳጆቼ! አምላክን ወልዶ መስጠት እንዲህ ቀላል ነገር
አይደለም፤ ዛሬ ጭንቅላታቸውን እንደስንደዶ አሹለው እኛም ለመመረጥ ብቁ ነን የሚሉና ወደ ሰማይ ያለ አቅማቸው እንደሚንጠራሩት ሴቶች
ጌታን መውለድ ለምድራዊ ክብርና ጉራ አይደለም፤ ጌታን ለመውለድ ሴት መሆን ብቻ በቂ አይደለም ከሴቶች ሁሉ መለየት እንዲሁም በዚያ
በጨለማው ዘመን እነ ኢሳያስና ኤልያስ ጻድቅ ብጹዕ ባልተባሉበት ዘመን በጸጋ ተመልቶ ከሰው ተለይቶ በተለየ ክብር መገኘት ያስፈልግ
ነበር፤ አንድ ጥይቄ ልጠይቅ፡- ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስራት ጸጋን የሞላብሽ
ሆይ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ የከበርሽ ነሽ ያላት መቼ ነበር? ጌታን ጸንሳ ወይስ ከመጸነሷ
በፊት? ወዳጄ! እመቤታችን ቀዳማዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በማህጸኗ ገና ሳያድን እነ ማኑሄን የገሰጸ መልዓክ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ
ነው ብላ እመቤታችን እስክትገረምና እስክትደነቅ ድረስ ለቀደሙት አባቶች ያልተሰጠው ክብርን ለዚያውም ከታላቅ መላዕክ አግኝታለች፤
ሁላችን ከጸጋ ጎድለን በነበረበት ጊዜ ላይ ጸጋን ጸሞልጋ የተገኘች እርሷ ናት፤ እመቤታችን አክብሩኝ አምላክን ካልወለድኩት ያለችው እርሷ ሳትሆን የመረጣት
ባለቤቱ እግዚአብሔር ነው እርሱ የወደደውንና የመረጠውን ደግሞ ማንም ሊያዋርደው ሊንቀው ክብሩንም ሊቀንስ አይችልም፤ ነገር ግን
አምላክ ራሱ ትህትናዋን አይቶ ከሰዎች ሁሉ አከበራት፡፡
ለምን
ሊቁ፣ አይሁዳዊ የለ አረማዊ በማርያም ያመነና
ስሟን የጠራ ይድናል ሕይወትንም ያገኛል አለ? በቅድሚያ ይህ ኃይለ ቃል የሰፈረበትን መጽሐፍ ስንመለከት፤ ይህ መጽሐፍ (መጽሐፈ ዚቅን) የጻፈው በነገረ መለኮት እውቀቱ የጠለቀው
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲሆን መጽሐፉም ቅኔያዊና ምስጢራዊ ሃሳቦችን በረቀቁ ቃላት የሚያስተላልፍ
የምስጋና መጽሐፍ ነው፡፡
አስቀድመን እንዳልነው አምላክ እንኳን ለአረማዊያን ለአይሁዳውያን ፤ እንኳንስ ለአይሁዳውያል ለከበሩት አባቶች ለአብርሃምና
ለሙሴ እንኳን አልታያቸውም ነበር እደግመዋለሁ እርሱን ማየት አልቻሉም ነበር፤ ፊቱን እየፋፈቁ ብቻ ኖረው ወደ መቃብር ተሸኙ እንጂ፤
ነገር ግን ከእመቤታችን ተወልዶ ተገለጸ፣ ጻየ፣ ሰው ሆነ ከሠማይም ሌላ ያመጣው ባዕድ ስጋ ወይ ከምድር የሆነ የወንድ ዘር የለም በረቂቅ ምስጢር በመንፈስ
ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችን መኅጸን ውስጥ እንደ ልጅ ተጸንሶ ደምና ምግብን እያገኘ ስጋን ከእርሷ ነስቶ ተወለደ የማይታየው
ታየ፤ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ ሙሴን እኔን አይቶኝ በህይወት የሚቆም ማንም የለም ያለ አምላክ አሁን በሚገርም ምስጢር በእርሷ በፊደላችን
ተነበበልን፤ ጌታን በኦሪት ሊያዩት የወደዱ ሙሴና ኤልያስ እንዲሁም አብርሃም በደብረ ታቦር ተራራ ድጋሚ መጥተው አዩት ደስም አላቸው፤
ስለዚህ አይሁዳዊ የለ አረማዊ ሕዝብ የለ አሕዛብ ያዩት ጌታችንን ያወቁት ከእመቤታችን ስጋን ነስቶ በመወለዱ ነው፡፡ ከእመቤታችን
ሲወለድ እንኳን ደጋግ አባቶችን ወገኖቹ አይሁዳውያን አረማውያን ሁሉ አዩት ሲል ነው፡፡
አመንም አላመንም፤
የእመቤታችን ክብር ሕግን በጽላት ላይ ቀርጾ ከሰጠን ከሙሴ፤ መጽሐፍትን ጽፈው ከሰጡን ከነብያት ይበልጣል! ለምን ከጽላቱ ጌታችነ
ከመጽሐፍቶቹም ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያህል እንዲከብር እንረዳለንና፤ መጽሐፍት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተረኩልን እንጂ በአካል አላስገኙልንም
አዳም 5500 ዘመን እየጓጓ በገሃነመ እሳት ውስጥ ቁጭ ያለው የጌታን ከእመቤታችን መወለድ (ልደቱን) በመጠባበቅ ነበር፡፡
በጌታ ልደት ማመን ደግሞ እንደ መናፍቃኑ በአስማት ወይ በድንገት ወረደ ሳይሆን የእኛን አርአያና ሰውነት ይዞ የአብርሃምን
ዘር ነስቶ ዘመን ቆጥሮ እንደ ሰው ተ . ወ . ለ . ደ ብሎ ማመን ነው! ቀጣይ ጥያቄው ከማን የሚለው ነው ስንጠየቅም መልሳችን
አንድና አንድ ነው የሚያደናግር ስሌት የለውም የነብያት እናቶች ብዙዎች ናቸው የሐዋርያትም እናቶች ብዛች ናቸው የጻድቃን የሰማዕታት
የአባቶችም እንዲሁ የአምላክ እናት ግን አንዲት ናት ስለዚህ ከማን ተወለደልን ስንባል የእናቱን የማርያምን ስም እንጠራለን፤ የእርሷን
ስም ስንጠራ ደግሞ ወላዲተ አምላክ ብለን ነው ይህም ማለት አምላክን የወለደች ማለት ነው፤ ስለዚህ እመቤታችንን ሰውን ፍጡርን ሳይሆን
ገናና፣ ክቡት፣ ኋያል፣ ኤልሻዳይ፣ አዶናይ፣ የሆነ ሰማይ ጣሪያው አንለው እርሱ ከእርሱም በላይ ያለ ወደ ታች ጥልቁ ዱዲያኖስ ከታቹ
የማንለው ከጨለማውም በታች እስከዚህ ላልተባለ ቦታ ያለ መላእክት እንኳን ምን ያህል ከአይን ጥቅሻ የፈጠኑ ከእሳት የረቀቁ ግሩም
ፍጥረታት ቢሆኑም ወደ ምስራቅና ምዕራብ ጌታችን የሌለበትን ቦታ የማያውቁት ታላቅ ጌታ ነው፤ ታዲያ ወገኖቼ
ይህም አምላክ በጠባቧ ማኅጸን የያዘችው ሰውነት አትደነቅም? ክብሯ አይገርማችሁም; ድፎ ዳቦን እንኳን ለማስቀመጥ መሶበ ወርቁን
ሰፋ አድርገን እንሰራለን ነገር ግን ታናሷ ሙሽራ አቻ የሌለውን ሙሽራ በጠባቧ ማህጸን አስተናገደችው! በኢሳያስ ዘመን ትንሽ ደመና
ተነስታ አህያ የማይችለው ዝናምን እንዳዘነመች በቁመት ሁለት ክንድ ከስንዝር የሆነች በቅድስናዋ ግን የከበረች እመቤታችን ዓለም
ሁሉ ጠጥቶ የረካበትን ውዳችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችልን፡፡
ስለዚህ የእመቤታችን ስምና ክብር በስተ ጀርባ ታላቅ ቁም
ነገር አለ፤ አምላክን የወደች የሚል ስም አላት እመ አምላክ አልናት ኢየሱስ አምላክ ነዋ፣ አምላክን ስለወለደች ወላዲተ
አምላክ እንላታለን፤ እመ አዶናይ እንላታለን ሁሉን ቻይ አምላክ
በግሩም ጥበቡ ከእርሷ ሰው ሆኗላ፤ አመ ብርሃን እንላታለን ከፊቱ ለአንዲት
ሰኮንድ ሽራፊ እንኳን ጨለማ የማያውቅ እውነተኛ አማናዊ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቷስን ያፈነጠቀች ምስራቅ አድርጓታላ፡፡
ስለዚህ ይህ የቅኔ መጽሐፍ በዚህች አጭር አረፍተ ነገር ውስጥ ምስጢረ ሥጋዌን ወይም (Christology)ን
በረቀቀ ምስጢራዊ ዘይቤ ገለጸው፤ በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ፍጡር ነው፤ እንዴት አምላክ የአብርሃምን ዘር ነስቶ ሰው ይሆናል ብለው
የእመቤታችን ጌታን መውለድ እርሱን እንደመፍጠር ይቆጠራል ብለው ክደው የድኅነታችንን ታሪክ አፈር ላይ ለማንከባለል የጣሩ፤ መጽሐፍ
ቅዱስን የተጻረሩ መናፍቃን ተነስተው ነበረ በ6ኛው ክፍለ ዘመን፤ በዚህ
ቃል ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የመለሰበት አንቀጽ ነው፤
አሁንም የእመቤታችንን ስም አስተካክለን ከጠራን የጌታን ስም አምላክ ነው ብሎ መጥራት ነው፤ እናቱ አምላክን ወለደች ማለት ልጇ
አምላክ ነው ብሎ ማመን ነው፡፡
የጌታን ስም የጠራ ይድናል አንጠራጠርም አዎ ይድናል ፤ የእመቤታችን ስም ላይ ደግሞ የጌታ ስም አለው፤ እንኳን የእመቤታችን
ስም ላይ አይደለም እመቤታችንን ያመሰገኗት መላዕክት ላይ ያበሰራት መልዐክ ላይ እንኳን ስሙ አለ ለዚህን አይደል እንዴ በእስራኤላውያን
ፊት መልአኩን እግዚአብሔር ሲልክ እንዳታስቆጡት ስሜ በእርሱ ላይ ነውና ይቀስፋችኋል ያለው፤ (ኤል) ማለት ኃይል ማለት ነው በዕብራይስጡ፤ ኃይል ማለት ደግሞ አምላክ፣ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማለት ነው፤
በዚህ ስም (ኤል) በሚለው ስም መላዕክት እስከዛሬ የሚደነቅ ኃይልን ተቀብለዋት፤
ታለቅ ኃይልና ማዕረግን ተሸክሞ የነበረውን ሳጥናኤልን እንደ መብረቅ ከሰማይ የጣሉበት ስልጣን ስም ኤል የሚለው ነው፤ የጌታ ስምን
መጥራት መዳን ብቻ አይደለም ከትንሳኤ በኋላ ለዘለዓለም ያለድካም እርሱን የምናመሰግንበት ኃይላችን ነው! ክብር ምስጋና ለእርሱ
ይሁን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም እግዚአብሔር ነውና የኢየሱስ ስም በሁሉም ቅዱሳን መላእክቱ ላይ አለ፤ የመላዕክቱ ስም ሲጠራ ሲሰማ
ጠካት ይደነግጣል ክርስቲያን ይደሰታል ደጋጎሞ ስሙንም በአምልኮው ውስጥ ይጠራል፤ ለምን የኃያሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስላለበት፤
እንደው መጽሐፍትን ከቁንጽል ጥቅስ ባሻገር ዞር ዞር ብለን አልተመለከትንም እንጂ በኦሪቱ በሙሴ ቢያምኑ ኖሮ ይድኑ ነበር ተብሎ
ተጽፏል፤ እረ ምን ማለት ነው በሉ; ጎበዝ መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ፤ ተከብሮ ደግሞ ያደርጋል ደንቆሮ ብዙ ሰዎችን ሰይጣን መላዕክት
ነኝ እያለ እየተገለጸላቸው ነው የልቦናቸውን በር በsecurity password የዘጋው፤ አምላኬ ምድን ነው ንገረኝ ካልነገርከኝ
አልለቅህም በራሴ ሃሳብ አልተረጉምም ማለት ያስፈልጋል፡፡ በሙሴ ማመን ማለት እግዚአብሔርን አለማመን አይደለም በጌታ ያመነ በወዳጆቹም
ያምናል፤ አላማቸው አንድና አንድ ነውና፡፡
የእመቤታችንንም ስም
መጥራት ጌታን መካድ አይደለም ይልቁን በእርሷ ፊደልነት ስጋን መልበሱንና ሰው መሆኑን መረዳት ነው፤ የኢየሱስን ስም ዝን ብለብ ከመጥራት በፊት ማንነቱን ተመረድተን መጥራት ያድናል፤ ለምን
ስሙን እኮ ጠላት ዲያብሎስም ጠርቶታል አይሁድ ጠርተውታል ሌሎቹም ነገር ግን የእንጨት ጠራቢው የዮሴፍ ልጅ ነው አሉ እንጂ የእግዚአብሔር
አብ የባሕሪ ልጁ ነው ብለው ስላላመኑ ተሰናክለው ወደ ቁበት አልዳኑበትም፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን ነው፤ የመዳናችን ምክንያት ደግሞ እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት!
ሔዋን ለሞታችን ምክንያት ሆና ሠይጣንን አማክራ ሞትን እንዳመጣችብን፤ እመቤታችን ደግሞ ከመልአኩ ጋር መክራ እነሆ ያለ ወንድ ከመንፈስ ቅዱስ መውለድ ከሆነ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችልን የመዳናችን ምክንያት ሆነችልን፤ የእርሱ መድኅን ደግሞ መዳኒትነቱ
ልዩ ነው ከነፍሳችን ቁስል ነው ያዳነን፡፡ እንዴ የኢያሱ እናት እንኳን ደስ ብሏታት
ነበር እኮ፤ እስራኤላውያንን ከጠላት አድኗቸው ነበርና፤ ኢያሱ ማለት የስሙ ትርጓሜ፤ መድኃኒት ማለት ነው፤ ኢየሱስ ማለትም እኮ መድኋኒት ማለት ነው፤ እና ሁለቱ አንድ ነው? አዳኝ የሚለውን ቃል
እኮ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ከመጀመሪያው መጽሐፍ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ብዙዎች ተጠቅሞበታል የኩሽ ልጅ ናምሩድ በምድር ሁሉ ላይ ኃያልና
አዳኝ ሆነ ይላል፤ ናዖድም ለእስራኤል አዳኝ ሆነ ይላል ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን መጽሐፈ ባልቴት ልንለው ነው? ከጌታ በቀር አዳኝ
የለም የሚለውን የተጻረረ ይመስለናላ እንዲያውም ነብዩ ዳንኤል ይውጣላችሁ ብሎን ይመስላል ከሊቀ መላእክት ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ
የለም ነበር ብሏል፤ ጎበዝ እናስተውል እዚህ ላይ ግን አንድ
ሃሳብ ልስጥ ወንድሞቼ፡- ያላመነና የጠላ ሰው አቃቂር ለማውጣት ወይም ለመተቸት ቅቤት በመርፌ እንደመውጋት ያህል ቀላል ነው፤ የጠላትን
ሚስቱን ባል የዛሬ ውኃሽ ቀጥኗል ብሎ ለጥል ይነሳል፤ ሙስሊሞቹ እኮ መጽሐፍ ቅዱስን
እንደ ጉድ ተችተውታል 1000 የመጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት፣ 6000 ስህተት እያሉ ከገጹ ብዛት ይበልጥ መጽሐፋችንን ይተቹብናል፤ እናም
ያላመንከውን መጽሐፍ ማጣጣል ቀላል ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስንም ካላመንክበት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሰላምን ሳይሆን ጦርነትን የሚሰብክ
መጽሐፍ ነው የሚመስልክ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የምንረዳው በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ነው የተከደነባቸው ለሚጠፉት ነው ይላላ፤ እነዚህም
የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት የጻፏቸው መጽሐፍት የዓለማቀፋዊት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ዶክትሪንና ስርዓተ
አምልኮን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እያብጠረጠረ የሚያስረዳ ስለሆነ ለሚያምን ብቻ
ነው የሚገባው፤ መንፈስ ቅዱስን አስተማሪ አድርጎ ወደ ልቡ ጠጋበዘ ብቻ ነው የሚጠቀምበት፤ ላላመኑና ለካዱት ግን የመሰናከያ ድንጋይ
የተከደነ መጽሐፍ ነው፤ በቅን እንረዳው እኛ ኦርቶዶክሳውያን ፈጽሞ እመቤታችን ተሰቅላ ሞታ አዳነችን ጌታን ትቶ የእርሷን ስም ብቻ
ጠርተን ገነት መንግስተ ሰማያትን እንወርሳለን ብለን አስተምረንም አስበነውም አናውቅም ያላሰብነውንና ያላልነውን በሉ ብላችሁ ካላስካዳችሁን
በቀር! ይልቅ ይሄ እኛ ሳናውቀው በድንኳን ውስጥ የተደረሰ የአሮጊቶች ተረት ተረት ነው፤ እኔ የሚገርመኝ ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ
አብሱ የሌለው እንደ ሞኝ ሁሉ ያይኔ አበባ አበባ . . . ያይኔ አበባን ያዘለ መሆኑ ነው፤ ክርስቲያኖች ዝም ብለን አንዳክር ኢየሱስ
ብቸኛ አዳኛችን ነው መዳን በሌላ በማንም የለም በጌታ ነው፤ እግዚአብሔር ብቻ አዳኝ ነው፤ ሌላ አማልክትን አናመልክም ነገር ግን
ቅዱሳኑ ምክንያተ ድህነት ናቸው ቅዱስ ሚካኤል ቢራዳን አምላከ ቅዱስ ሚካኤል ተመስገን ብለን ባለቤቱን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፤
እንጂ አምላክን ጥለን ሌላ አላንጠለጠልንም አምላክንም ቅዱሳኑንም እንደ መጽሐፉ ቃል እንቀበላቸዋለን፤ ለምን እናንተን የተቀበለ
እኔን ይቀበላን እናንተን ያልተቀበለ እኔንም አይቀበልም በወልድ ያላመነ ደግሞ አብም መንፈስ ቅዱስም የለውም!!!! ይልብናል ማቴ
10፡ እግዚአብሔር እኮ እንደ ስግብግብ ባለስልጣን ክብሬን ለሌላ አልሰጥም ስልጣን አላጋራም የሚል ዲክታቶር አይደለም እኛ ነን
እንደዚህ እያደረግ ነው ያለነው፤ አንዳንዶች ጌታን ብቻ ያሉ መስሏቸው እርሱ ተቀበሏቸው ያለንን ጻድቃንና ሰማዕታትን መጣል ጌታንም
መጣል ነው፤ እርሱ ብርሃን ሆኖ እኛን እናንተ የአለም ብርሃን ናችሁ ያለ እርሱ ደግ እረኛ ሆኖ የእረኝነትን ስራ ለሰዎች የሰጠ
ፈራጅ ሳለ በ12ቱ ወንበሮች ተቀምጣችሁ ትፈርዳላችሁ ብሎ ለሐዋርያቱ ስልጣንን የሰጠ እርሱ ራሱ ጌታችን ነው አንስማማም ካልን እንግዲ
መጽሐፉን መፋቅ በማይገባ ቋንቋ መተርጎም ሳይሆን እንዳለ ሆኖ እርሱን መጠየቅ ነው ይገልጽልናል፤ አልያ ከመውጊያ ብረቱ ጋር መታገል
ነው፤
ስለዚህም የእርሱን
ስም ፍጡር ካልነው ብቻ የእመቤታችን ስም አይለወጥም ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እስከሆነ ድረስ፤ አዳኝ እስከ ሆነ ድረስ
እመቤታችንም የእርሱ እናት ነች፤ የአማልክ የአዳኙ እናት ነች! ስሟም የድኅነትን ኃይል ያዘለ ነው የሚሆነው፡፡
በመጨረሻም፤
ከጌታ በቀር አዳኝ የለምና ሌሎቹንም የመጽሐፍትን ቃላት በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ካልተረዳን አደጋ ነው! በቀርከሃ ሸንበቆ እያዩ
ፈረስ እንደመጋለብ ይቆጠራል ያ ደግሞ መጨረሻው ገደል መግባት ነው፤ ለምሳሌ ሌላ ቤዛ የለም የተቤዠንም የለም ብለናል፤ ሌላ ቦታ
ላለ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ቤዛ ሆኛችኋለሁ ተቤዝቻችኋለሁ ይለናል፤ ወገኖቼ! አሁን ችግር የሆነው በራሳችን ስሜት መተርጎማችን
ነው እንዲህ ከኖነ ደግሞ ከክርክርና ጭቅጭቅ ሳንወጣ ዘላለም እንደማይግባቡ ባልና ሚስት ከራሳችን ጋር እየተ ተናከርን ነው ዘመናችንን
የምንገፋው እንኳን መጽሐፈ ዚቅን መጽሐፍ ቅዱስም መቀበል የግድግዳ ዳገት ነው የሚሆንብን፤ ሐዋርያው ግን የተቤዠን ነጻ የሚያወጣውን
የኢየሱስ ክርስቶስን ቃሉን ስለሰጠን ስላስተማረን ተቤዠን፤ ታዲያ ማን አዚም አድርጎብን ነው አይናችንን አሳውሮን ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስ ቃሉን ስላስተማረን ተቤዠን ስንል እመቤታችንን Logos አካላዊ ቃልን አስገኝታልን የመድኃኒት እናት ለማለት አፋችን እንደ
6 ወር ሕፃን የሚረሳሰረው፤ እግዚአብሔር ልቦናን ይስጠን፤ ይግለጽልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ይቆየን. . .